በካናዳ የሚኖሩ ዳያስፖራዎች ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ86 ሺህ ዶላር በላይ ድጋፍ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
በካናዳ የሚኖሩ ዳያስፖራዎች ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ86 ሺህ ዶላር በላይ ድጋፍ አደረጉ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 23 / 2013 (ኢዜአ) በካናዳ የሚኖሩ ዳያስፖራዎች ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል ከ86 ሺህ በላይ የካናዳ ዶላር ድጋፍ አደረጉ።
ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ "ጥምረት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ" የቫንኩቨርና የሳስካቹዋን ግዛቶች በካናዳ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በመተባበር በሳምንቱ መጨረሻ በበይነ መረብ ባካሄዷቸው የገቢ ማሰባሰቢያ መድረኮች ድጋፉን አድርገዋል።
በዚህም በቫንኩቨር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያኑና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለግድቡ ግንባታ 64 ሺህ 500 የካናዳ ዶላር ማሰባሰባቸውን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ይፋ አድርጓል።
በተመሳሳይ በሳስካቹዋን ግዛት የሚኖሩት ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በካናዳ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በመተባበር በሳምንቱ መጨረሻ ባካሄዱት የገቢ ማሰባሰቢያ መድረክ ከ22 ሺህ በላይ የካናዳ ዶላር ለግሰዋል።የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት፤ በካናዳ የሚኖሩ ዳያስፖራዎች ለአገራዊ ፕሮጀክቶችና ለወቅታዊ ጥሪዎች እያደረጉት ላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
በሕጋዊ መንገድ ብቻ የውጭ ምንዛሪን ወደ አገር ቤት በመላክ ለአገራቸው ያላቸውን ድጋፍ በተግባር ማሳየት ይጠበቅባቸዋልም ብለዋል።
በካናዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ፤ ዳያስፖራው ለግድቡ ግንባታ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበው፣ ግንባታው እስኪጠናቀቅ እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።
"ጥምረት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ" የቫንኩቨር ክፍል (ቻፕተር) ሰብሳቢ ዶክተር ገብረህይወት ልብሰቃል በውይይቱ ላይ እንደተናገሩት ጥምረቱ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ 20 ሺህ የካናዳ ዶላር ማሰባሰቡን ገልጸዋል።በቀጣይም ዳያስፖራው ድጋፉን እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የተደራዳሪ ቡድን አባል አቶ ዘሪሁን አበበና የውሃ ሳይንስ ተመራማሪዋ ወይዘሪት መቅደላዊት መሳይ ከአባይ ወንዝ አጠቃቀምና ከሶስትዮሽ ድርድሩ ጋር በተያያዘ በመድረኩ ላይ ጽሁፎችን አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል።