የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ህንጻ በጎርፍ ከተጎዳ ሁለት ዓመት ቢሆነውም መፍትሄ አልተሰጠውም - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ህንጻ በጎርፍ ከተጎዳ ሁለት ዓመት ቢሆነውም መፍትሄ አልተሰጠውም
አዲስ አበባ ሐምሌ 27/2010 ንብረትነቱ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የሆነው በቃሊቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የሚገኘው ከሃያ በላይ ክፍሎች ያሉት ህንጻ በጎርፍ ጉዳት ደርሶበት ከሁለት ዓመታት በላይ ያለ አገልግሎት ተቀምጧል። ህንጻው ተገቢውን የጥገና አገልግሎት አግኝቶ ለስራ እንዲውል የተደረገ ጥረት አለመኖሩም ተገልጿል። ተቋሙ ከ20 በላይ ክፍሎች ያሉትን ህንጻው ለተለያዩ ተቋማት የቢሮ አገልግሎት አከራይቶ በየዓመቱ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ገቢ ያገኝ እንደነበርም ተጠቁሟል። ነገር ግን ህንጻው በ2008 ዓ ም በጎርፍ ተውጦ አገልግሎት መስጠት ማቆሙን በድርጀቱ ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች መታዘባቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልገሎት ድርጅት የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ የኋላወርቅ ጎሹ እንዳሉት ችግሩ ከተጠቀሰው ጊዜ ጀምሮ መከሰቱንና ህንጻውን ተከራይቶ የነበረው የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ጉዳቱን ተከትሎ ለቆ መውጣቱን አረጋግጠዋል። ህንጻውን ያጥለቀለቀው ውሃ ከየት እንደሚመጣ ማወቅ እንዳልተቻለ የተናገሩት ዳይሬክተሩ የጎርፍ ማስተላለፊያ ቱቦ በመፈንዳቱ ችግሩ እንደተከሰተና እየተባባሰ መጥቶ ከዚህ ደረጃ መድረሱን ገልጸዋል። ችግሩን ለመፍታትም ለአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን በደብዳቤ ተጠይቆ ወረፋ እንዲጠብቁ በመገለጹ ችግሩን በአፋጣኝ መፍታት እንዳልተቻለ ተናግረዋል። ሃላፊው ይህን ይበሉ እንጂ በህንጻው ላይ የደረሰውን ጉዳት ለማስተካከል ይህን ያህል ጊዜ ሊወስድ የሚችል ባለመሆኑ የሚመለከተው አካል ስራውን በትኩረት መስራት አለመቻሉን ነው አስተያየት ሰጪዎቹ የሚናገሩት። ችግሩን ለሚመለከተው አካልና ለዋናው መስሪያ ቤት ቢያሳውቁም አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጠው ከማድረግ አንጻር እንቅስቃሴው ደካማ መሆኑን አንስተዋል። እንደ አቶ የኋላወርቅ ተቋሙ ችግሩን በራሱ አቅም ለመፍታት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ጋር ጥረት እያደረገ መሆኑንና በቅርብ ጊዜ ውስጥ እልባት ሊያገኝ እንደሚችል ገልጸዋል።