በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የሚገቡ አገራት ከድርጊታቸው እንድታቀቡ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪ አቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የሚገቡ አገራት ከድርጊታቸው እንድታቀቡ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪ አቀረበ
አዲስ አበባ ግንቦት 23 ቀን 2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የሚገቡ አገራት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ሲል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪ አቀረበ።
ቅዱስ ሲኖዶሱ ከግንቦት 17 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ሲያካሄድ የቆየውን ጉባኤ አጠናቋል።
የጉባኤውን ማጠቃለያ አስመልክተው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያሥ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ኢትዮጵያ በዘመናት ዳር ድንበሯን ጠብቃና አስጠብቃ ያለ ቅኝ ግዛትና ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት አንድነቷን ጠብቃ የቆየች ሀገር መሆኗን ጠቅሰዋል።
ሆኖም በአሁኑ ጊዜ አንዳንድ የውጭ አገራት ከሩቅና ከቅርብ ግንባር በመፍጠር በአገሪቷ ሕልውና ላይ እያደረጉት ያለውን ጣልቃ ገብነት እንዲያቆሙ ቅዱስ ሲኖዶሱ ማሳሰሰቡን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያዊያንም ከምንጊዜውም በተለይ አገራዊ አንድነታቸውን ከውጭ ወራሪና ጣልቃ ገብነት በመጠበቅ በጋራ እንዲቆሙም ጥሪ ቀርቧል።
ኢትዮጵያ ማንኛውንም አገር ሳትጎዳ በተፈጥሮ ሃብቷ ለመልማት የምታከናውናቸው ስራዎች በየትኛውም ሃይል ሊደናቀፍ አይገባውም ብለዋል።
በመሆኑም በልማት ለማደግና ዜጐቿን ከጨለማ ለማውጣት የምትገነባው የህዳሴ ግድብ ከዳር እንዲደርስ የሁሉም ድጋፍና ትብብር አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
በምርጫው የሚመጣውን ውጤት ሁሉም አካል በፀጋ በመቀበል ኢትዮጵያዊ ጨዋነት የሚታይበት ምርጫ እንዲሆንም ጉባኤው የሰላም ጥሪውን አቅርቧል፡፡
ኢትዮጵያዊያንም ለአገርና ለህዝብ ይበጃል የሚሉትን እንዲመርጡና ለምርጫው ሰላማዊነት የበኩላቸውን እንዲወጡ ቅዱስ ፓትሪያሪኩ አሳስበዋል፡፡
በአገሪቷ በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠረው አለመግባባት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኞችን ማሰብ እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡
በተለመደውና በኖረው የመረዳዳትና የመተሳሰብ ባሕልም ከምንግዜው በላይ ለችግራቸው መድረስ እንደሚገባ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን አቅርቧል።
በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት በጐንቻ ሲሶ እነሴ ወረዳ በምስካበ ቅዱሳን ቆጋ ኪዳነምሕረት በሕገ-ወጥ መንገድ የቤተ-ክርስቲያኗን ዶግማና ቀኖና በጣሰ መልኩ ራሳቸውን በራሳቸው ጳጳስና ፓትርያርክ አድርገው የሾሙ መምህር ሄኖክ ፈንታ፣ መምህር አባ ኪዳነማርያም እና መሪጌታ ሙሉን ከግንቦት 19 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ መወገዛቸው ተገልጿል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ከግንቦት 17 እስከ ግንቦት 23 ዓ.ም ለስድስት ቀናት ሲያካሂድ የቆየውን ጉባኤ አጠናቋል፡፡