ቀጥታ፡

ምርጫውን ካሸነፈ ለህዝቦች እኩልነት እንደሚሰራ አብን ገለጸ

ደብረ ብርሃን፤ ግንቦት 23/ 2013(ኢዜአ) የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ(አብን) በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ካሸነፈ ለዘላቂ ሰላምና እና ለህዝቦች እኩልነት እንደሚሰራ ገለጸ።

ፓርቲው "ግዜው አሁን ነው" በሚል መሪ ሀሳብ በደብረ ብርሃን ከተማ የምርጫ ቅስቀሳ አካሄዷል።

የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ የሱፍ ኢብራሂም በወቅቱ እንደተናገሩት፤ አብን በምርጫው ቢያሸንፍ ሰላም የሰፈነባት ኢትዮጵያን በመገንባት ሁሉም ዜጋ በእኩልነት እንዲኖርባት ይሰራል።

ፓርቲው የሃገሪቱን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ መለወጥ የሚያስችሉና የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ አማራጭ ፖሊሲዎችን ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ገልጸዋል።

ድህነትና ሥራ አጥነትን በመቀነስ የዜጎችን ህይወት ለማሻሻልም አበክሮ እንደሚሰራም ነው ያስታወቀው። ምርጫው በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ህዝቡ ድምጹን በሚሰጥበት እለት እራሱን እና ቤተሰቡን ከኮሮና ቫይረስ በመጠበቅ መሆን እንዳለበት ጠቁመው፤ የአብን የምርጫ ምልክት ሰዓት መሆኑን ገልጸዋል።

የፓርቲው የሰሜን ሸዋ ዞን ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጌታሁን ሳህለ በበኩላቸው፤ፓርቲው አባላቱን በማስተባበር ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆንና ህዝቡ በምርጫው እለት ወጥቶ ድምጹን እንዲሰጥ የግንዛቤ ፈጠራ ስራ እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም