ቀጥታ፡

የፕሪሚየር ሊጉ አክሲዮን ማኅበር ተጫዋቾችን ለማዘዋወር የተቀመጠው የደመወዝ ጣሪያ እንዲነሳ ወሰነ

ግንቦት 22/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የሊጉን ተሳታፊ ክለቦች ተጫዎቾች ለማዘዋወር የተቀመጠው 50 ሺህ ብር የደመወዝ ጣሪያ ገደብ እንዲነሳ ወሰነ።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ዛሬ አካሂዷል።

ጉባኤው የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ተጫዎቾችን ለማዘዋወር የተቀመጠው 50 ሺህ ብር የደመዝ ጣሪያ ገደብ ዙሪያ፣ የዳኞችና ኮሚሽነሮች የውሎ አበል ማሻሻያ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።

እንዲሁም ከቴሌቪዥን ቀጥታ ስርጭትና ስያሜ ከተገኘው 4 ሚሊዮን ዶላር የፕሪሚየርሊግ ተሳታፊ ክለቦች የሚያገኙት የገንዘብ መጠንም ይፋ ሆኗል።

ጉባኤውን የመሩት የአክሲዮን ማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ የተጫዋች የደመወዝ ጣሪያ መቀመጡ ከጅምሩም ህገወጥ መሆኑንና ክለቦችንም ለተለያዩ ችግሮች መዳረጉን አስታውሰዋል።

በአገሪቷ የተጫዋቾች ዝውውር ፕሮፌሽናል አካሄድ እንዳይኖረው በማድረግና በተጫዋቾችና ክለቦች መካከል በየጊዜው አለመግባባት እንዲፈጠር በማድረግ ውድድሩ ላይ ተፅእኖ ማሳደሩንም አንስተዋል።

በክለቦችም በኩልም መመሪያ መቀመጡ ህገወጥ ከመሆኑ በተጨማሪ በአብዛኞቹ ክለቦች በትክክል ተግባራዊ እየተደረገ አለመሆኑን ጠቁመዋል።

በአብዛኞቹ ክለቦች በመመሪያ የተቀመጠውን የደመወዝ መጠን የውል ወረቀት ላይ እንጂ በውስጥ ተጨማሪ ገንዘብ ለመክፈል ድርድሮች መኖራቸውን ነው የተናገሩት።

ይህም የተጫዋቾች የደመወዝ ጣሪያ ከእግር ኳሱ እድገት በላይ እንዳይሆን ታስቦ የወጣውን ዓላማ ከማሳካት ይልቅ መንግስት ማግኘት ያለበትን ግብር እንዲያጣ አድርጓል ብለዋል።

ችግሩን ለመፍታት በቀጣይ ተጫዋቾችን እንደ አቅማችው የደመወዝ ገደብ ሳይደረግባቸው እንዲያስፈርሙ ውሳኔ ተላልፏል።

በጉባኤው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከሌላው ዓመት በተለየ የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት እንዲያገኝ በመደረጉና ስያሜው በመሸጡ ከዲ.ኤስ.ቲቪ ከተገኘውን 4 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ክለቦች የሚያገኙት የገንዘብ መጠንም ይፋ ሆኗል።

ከተገኘው 4 ሚሊዮን ዶላር ገቢ 60 በመቶ ያህሉን ሁሉም ክለቦች እኩል የሚካፈሉ ሲሆን 25 በመቶውን ደግም እንደየውጤታቸው ቅደም ተከተል ይደርሳቸዋል ነው የተባለው።

በዚሁ መሰረት ሻምፒዮኑ ፋሲል ከነማ 10 ሚሊዮን 346 ሺህ ብር ገቢ ያገኛል ተብሏል።

ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ኢትዮጵያ ቡና 10 ሚሊዮን 169 ሺህ፣ ሶስተኛ ደረጃን የያዘው ቅዱስ ጊዮርጊስ 9 ሚሊዮን 991 ሺህ ብር ያገኛሉ።

ከፕሪሚየር ሊጉ የተሰናበቱ ክለቦችም እንደየደረጃቸው ቅደም ተከተል እስከ 8 ሚሊዮን ብር ገቢ ያገኛሉ።

ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ለወጡት ፋሲል ከነማ 1 ሚሊዮን ብር፣ ኢትዮጵያ ቡና 700 ሺህ ብር እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ 500 ሺህ ብር ተጨማሪ የገንዘብ ሽልማት እንደሚያገኙም ተገልጿል።

ጉባኤው የዳኞችና ኮሚሽነሮች ውሎ አበል ከ1 ሺህ ወደ 2 ሺህ ብር ከፍ እንዲል የወሰነ ሲሆን የሙያ አበላቸው ባለበት 3 ሺህ ብር እንዲቀጥል ወስኗል።

የ2013 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ ከሌላው ጊዜ በተለየ በዲ.ኤስ.ቲቪ የቀጥታ የቴሌዥን ስርጭት ያገኘበት ሲሆን በዓመቱ ከተካሄዱ 156 ጨዋታዎች 153 የፕሪሚየርሊጉ ጨዋታዎች የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት አግኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም