ወሳኙን ምዕራፍ በድል በመሻገር የኢትዮጵያን ታላቅነት እንደምናስቀጥል ለዓለም እናስመስክር - ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ግንቦት 22/2013 (ኢዜአ) የምንገኝበትን ወሳኝ ምዕራፍ በድል በመሻገር የኢትዮጵያን ታላቅነት የምናስቀጥል ትውልድ መሆናችንን ዳግም ለዓለም እናስመስክር ሲሉ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስገነዘቡ።

"ድምፃችን ለነፃነታችንና ለሉዓላዊነታችን" በሚል መርህ በአዲስ አበባ ስታዲየም ሠላማዊ ሰልፍ ተካሂዷል።

ሠላማዊ ሰልፉ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የውጭ ሃይሎች ጣልቃ ገብነትን ለማውገዝና ወጣቶች ለአገራቸው ድምጻቸውን ለማሰማት የተዘጋጀ ነው።

የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታና ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌትን አስመልክቶ እየተፈጠሩ ያሉ ጫናዎችን በመቃወመም ተካሂዷል።

በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደው በዚህ ንቅናቄ ወጣቶች "በአገራችን ጉዳይ ጣልቃ አትግቡ"፣ "እኛ ወጣቶች በአገራችን ጉዳይ አንደራደርም"፣ "አባቶቻችን በነፃነት ያቆዩዋትን አገር በእኛም ተከብራ ትቀጥላለች" የሚሉ መልዕክቶችን አስተጋብተዋል።

"እኛ ወጣቶች የአገራችንን ሉዓላዊነት እናስከብራለን"፣ "አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የጣለችውን ማዕቀብ እንቃወማለን"፣ "የእኛን መሪዎች እኛ እንመርጣለን" የሚሉ መልዕክቶችም ተስተጋብተዋል።

በሠላማዊ ሰልፉ ላይ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች፣ የመዲናዋ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና እንግዶች ተገኝተዋል።

ማህበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴና ጥሪ የተደረገላቸው

ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባስተላለፉት መልዕክት ወጣቶች አገራቸውን ላለማስደፈር የውጭ ሃይሎችን ጣልቃ ገብነትና የውስጥ ባንዳዎችን በጋራ መታገል እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

የውስጥ ባንዳዎች ከውጭ ሀይሎች ጋር በማበር ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣት የምታደርገውን ጥረት ለማደናቀፍ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በጥቁር ሕዝቦች ታሪክ ለውጭ ሃይሎች ተንበርክካ አታውቅም ያሉት ምክትል ከንቲባዋ አሁንም የውጭ ሃይሎችን ጣልቃ ገብነት እንደማትቀበል አስታውቀዋል።

የአገሪቷን የውስጥ ሠላም ማስጠበቅ የሕዝቦቿ ዋነኛ ተግባር መሆኑን በመጠቆም ዛሬም የአባቶቻችን ድል እንዲደገም በጋራ መቆም አለብን ብለዋል።

በአገር መከላከያ ላይ ክህደት የፈፀመውን፣ በማይካድራ  ዜጎችን በመጨፍጨፍና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሽብር ሴራ በማስተባበር የኖረውን አሸባሪውን ህወሓት ማስወገድ ድጋፍ እንጂ ነቀፌታ አያስፈልገውም ሲሉም ተናግረዋል።

አሜሪካና አጋሮቿ በሉዓላዊት አገር ጣልቃ በመግባት የሚያደርጉት ተጽእኖ ተቀባይነት እንደሌለውም አስታውቀዋል።

ምክትል ከነቲባ አዳነች አቤቤ ወጣቶች 6ኛው አገራዊ ምርጫ ሠላማዊና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሚጠበቅባቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

'ወጣቶች ምርጫውን ካርዳችሁን እንጂ ህይወታቸውን የማትሰጡበት እንዲሆን ማድረግ አለባችሁ' ሲሉ ተናግረዋል።

ጥቃቅን ልዩነትና ጥርጣሬን አስወግደን ዋና መዋጊያ መሳሪያችን ኢትዮጵያዊ አንድነት መሆኑን መረዳት ይገባናል ብለዋል።

ይህን ወሳኝ ምዕራፍ በድል በመሻገር የኢትዮጵያን ታላቅነት የምናስቀጥል ትውልድ መሆናችንን ዳግም ለዓለም እናስመስክር ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ በበኩላቸው፤ ጀግኖች አርበኞች ለአገራቸው መስዋዕትነት በመክፈልና ዘብ በመቆም ነፃና ሉዓላዊ  አገር ለትውልድ ማስረከባቸውን አስታውሰዋል።

ወጣቶች አሁንም የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብና ሉዓላዊነቷም እንዳይደፈር ለአገራቸው ዘብ እንዲቆሙ ጥሪ አስተላልፈዋል።

"እኛ አንድ ከሆን ማንም አይደፍረንም" ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የአዲስ አበባ ወጣቶችና በጎ ፍቃድ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብርሃም ታደሰ በበኩላቸው፤ ወጣቶች የውስጥና የውጭ ጠላቶችን በሚያሳፍር መልኩ በአንድነት ቆመናል ብለዋል።  

በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ባለቤትና ወሳኞች እኛው ብቻ ነን ያሉት አቶ አብርሃም ወጣቶች በብሔራዊ ጥቅማችንና በአገራችን ሉዓላዊነት አንደራደርም ነው ያሉት።

ሠላማዊ ሠልፈኞቹ የውጭ ሃይሎችን ጣልቃ ገብነትና በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታና ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌትን አስመልክቶ እየተፈጠሩ ያሉ ጫናዎችን አውግዘዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም