ቀጥታ፡

አቶ ርስቱ ይርዳው በሚወዳደሩበት የምርጫ ክልል የብልጽግና ፓርቲ የድጋፍ ሰልፍ ተካሄደ

ግንቦት 22/2013 (ኢዜአ) የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳ በሚወዳደሩበት የምርጫ ክልል የብልጽግና ፓርቲ የድጋፍ ሰልፍ ተካሄደ።

በክልሉ ጉራጌ ዞን እነሞርና ኤነር ምርጫ ክልል ላይ ብልጽግና ፓርቲን በመወከል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩት አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ እንዲሁም ለክልል ምክር ቤት የሚወዳደሩት አቶ ርስቱ ይርዳው፣ ወይዘሮ ፈትያ ዮሐንስ እና ጌታሁን ነጋሽ በድጋፍ ሰልፉ ላይ ተገኝተዋል።

የድጋፍ ሰልፉ ተሳታፊዎች አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል ለሚችል አካል ድምጻቸውን ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ባሰሙት መፈክር ገልጸዋል።

ሰልፈኞቹ በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገውን የውጭ የኃይሎችን ጫና በማውገዝ ፤ አገራዊ አንድነት በማጠናከር ጫናውን ለመመከት የድርሻውን እንደሚያበረክቱ አረጋግጠዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአገሪቱ ልማት ወሳኝ ፕሮጀክት መሆኑን የገለፁት ሰልፈኞቹ፤ ለግድቡ ግንባታ ከፍጻሜ መድረስ በገንዘብ፣ በሀሳብና በጉልበት ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

እጩ ተወዳዳሪዎቹ በምርጫው ካሸነፉ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን እንደሚያስቀጥሉ ገልፀው፤ የህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ እንደሚሰሩም በመግለፅ ቃል ገብተዋል።

የኢትዮጵያን መልማት የማይፈልጉ ኃይሎችን ለማሸነፍ ወንድማማችነትን በማጠናከር ወደ ብልጽግና መጓዝ ብቸኛ አማራጭ መሆኑንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም