ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ-ጅቡቲ የትራንስፖርት ኮሪደር አካል የሆነው የአዳማ-አዋሽ 60 ኪሎ ሜትር የፍጥነት መንገድ ግንባታ ተጀመረ

ግንቦት 22/2013 (ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ የኢትዮጵያ-ጅቡቲ የትራንስፖርት ኮሪደር አካል የሆነውን የአዳማ-አዋሽ ምዕራፍ አንድ 60 ኪሎ ሜትር የፍጥነት መንገድ ግንባታን በይፋ አስጀመሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያን በአራቱም አቅጣጫ ከሚገኙ ጎረቤት አገራት መንገድን ጨምሮ በሁሉም መስክ ለማስተሳሰር በትኩረት እየተሰራ ለመሆኑ ፕሮጀክቱ ጉልህ ማሳያ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ግንባታው ዛሬ የተበሰረው የኢትዮ-ጅቡቲ የትራንስፖርት ኮሪደር አካል በመሆኑ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፋይዳ እንዳለውም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ 'ቀን ከሌት እየሰራ የአባቱን ሐብት የሚያበዛ ወጣት ትፈልጋለች' ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወቅቱ 'የልማት ስኬትን በማረጋገጥ ወደ ለውጥ የምንሸጋገርበት በመሆኑ እጅ ለእጅ ተያይዘን ለስራ እንነሳ' ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የመንገዱ ግንባታ ሲጠናቀቅ ከጅቡቲ ጋር ያለውን ዘመናትን ያስቆጠረ የኢኮኖሚና የንግድ ግንኙነት ከየትኛውም ጊዜ በተሻለ ፈጣንና ዘመናዊ እንደሚያደርገውም ገልጸዋል።

የፍጥነት መንገዱ ከጅቡቲ ወደብ ነዳጅ በመያዝ አዋሽ ማጠራቀሚያ ዴፖ ከሚያገናኘው የባቡር መስመር የማራገፊያና የመጫኛ ስፍራ ጋር በቅርብ ርቀት የሚገናኝ በመሆኑ ወደተለያዩ አካባቢዎች የሚደረገውን የነዳጅ አቅርቦት የሚደግፍ ይሆናል ብለዋል።

ሚኒስትሯ መንገዱ የትራንስፖርት ፍሰት መጨናነቅ ላይ ለውጥ የሚያመጣና ከአንድ ሠዓት ተኩል በላይ ይወስድ የነበረውን ጉዞ ወደ 30 ደቂቃ ዝቅ የሚያደርግ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።

ይህም በንግዱ ዘርፍ የሠዓት አጠቃቀምን ተከትሎ የሚደርስ ኪሳራን ለማስቀረትና ፈጣን እድገት ለማስመዝገብ አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን አክለዋል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ የኢትዮጵያ ተጠሪ ዶክተር አብዱል ካማራ በበኩላቸው ባንኩ በኢትዮጵያ ለሚከናወኑ ሰፋፊ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ግንባታው የደረቅ ወደብ አገልግሎቱን ከፍ ወዳለ ደረጃ እንደሚያሸጋግረው እምነታቸው መሆኑን በመግለጽ 'ለስኬቱ አብረን እንሰራለን' ብለዋል፡፡

በአዳማ በተካሄደው የመንገድ ፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አደም ፋራህ፣ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ፣ የሱማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ፣ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኘ እንዲሁም ከፍተኛ የፌዴራልና የክልል ባለስልጣናትና እንግዶች ታድመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም