በየትኛውም የውጪ ጫና የህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌትና ሀገራዊ ምርጫው አይደናቀፍም... የአሶሳ ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
በየትኛውም የውጪ ጫና የህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌትና ሀገራዊ ምርጫው አይደናቀፍም... የአሶሳ ወጣቶች
አሶሳ፤ግንቦት 22/2013(ኢዜአ )የትኛውም የውጪ ጫና የህዳሴው ግድብ 2ኛ ዙር የውሃ ሙሌትና 6ኛውን ሃገራዊ ምርጫ አያደናቅፈውም ሲሉ የአሶሳ ከተማ ወጣቶች ዛሬ ባካሄዱት ሰልፍ ገለጹ።
ወጣቶቹ “ድምጻችን ይሰማ” በሚል መሪ ሀሳብ በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገውን የውጪ ጣልቃገብነት በመቃወም ዛሬ በአሶሳ ከተማ ሠላማዊ ሰልፍ አካሄደዋል፡፡
በሠላማዊ ሰልፉ ከተሳተፉት መካከል ወጣት ፈዱል አብዱልመጂድ ለኢዜአ እንዳለችው በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ የሚደረግ የውጪ ጣልቃገብነት አግባብነት የለውም፡፡
"የህዳሴው ግድብ እንዳይጠናቀቅ የሚደረገው ሴራ የክልሉን ህዝብ በእጅጉ አስቆጥቶታል" ብላለች፡፡
"የህዳሴው ግድብን ጨምሮ የኢትዮጵያ ደህንነት እኛ በሕይወት አያለን አይደፈርም" ያለችው ወጣቷ፤ ይህን አቋም ለዓለም ለማሳወቅ ከነልጇ በሠላማዊ ሰልፍ መውጣቷን ተናግራለች፡፡
ወጣት እርቅነው አማረ በበኩሉ አሜሪካ የጣለችው የቪዛ ክልከላ ፈጽሞ አግባብ የሌለው እንደሆነ በመግለጽ፤ "ኢትዮጵያ የራሷ ሉአላዊነት ያላት በምንም መልክ የማትደፈር ናት" ብሏል።
ማንኛው ጣልቃ ገብነት ሁለተኛውን የህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌትና 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ እንደማያደናቅፍም የገለጸው ወጣት እርቅነው፤ "በሀገሪቱ ጉዳይ ጣልቃ የሚገቡ አካላት ይህንን እንዲረዱልን ለማድረግ ድምጻችንን ለማሰማት ሰልፍ ወጥተናል" ነው ያለው።
"ከአባታችን የወረስነውን ጀግንነት ለ21ኛው ክፍለ ዘመን በሚመጥን መልኩ በስራ ለማስቀጠል ተዘጋጅተናል" ብሏል፡፡
በተሰማራንበት የስራ መስክ ሁሉ ለሃገር የሚጠቅም ውጤት በማስመዝገብ ከእርዳታ ተላቀን በራሳችን የምንቆምበትን ሁኔታ መፍጠር ይገባልም በማለት ገልጿል።
በተለይ ወጣቱ ስራ ፈጣሪነቱን በማጠናከር የሃገሩን ሉአላዊነት ማስጠበቅ እንዳለበትም ይጠቅሳል።
ኢትዮጵያ እንዲትደፈር ስለማንፈልግ "ድምጻችን ይሰማ" በሚል በአንድነት ተነስተናል ያለችው ደግሞ ወጣት ወይንሸት ታምሩ ናት፡፡
"አባቶች የከፈሉልንን መስዋዕትነት ለማጽናት ቆርጠን ተነስተናል" ብላለች።
ወጣቶቹ በሰላዊ ሰልፉ ማጠቃለያ ኢትዮጵያ ለአፍሪካም ሆነ ለዓለም ሠላም መስዋዕትነት እየከፈለች መሆኗን ጠቅሰው፤ "መንግስትና ህዝብ አሸባሪ ብሎ ከፈረጃቸው አካላት ጋር ድርድር እንዲካሄድ የሚደረገውን ጫና በእጅጉ እንቃወማን" ብለዋል፡፡
ይልቁንም መንግስት ተፈናቃዮችን መልሶ በማቋቋም ሀገርን ለማረጋጋት የሚያደርገውን ጥረት አሜሪካና ሌሎችም ሀገራት መደገፍ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡
ሀገር ሲዘርፉና ዜጎች እንዲሰደዱ ሲያደርጉ የኖሩ አካላት ለፍርድ እንዲቀርቡ ከመንግስት ጋር አብረው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ግብጽና ሱዳን የኢትዮጵያውያን የዓይን ብሌን የሆነውን የህዳሴ ግድብ ለማደናቀፍ የሚያደርጉትን ጫና ትተው ለጋራ ተጠቃሚነት እንዲሰሩም ወጣቶቹ ጠይቀዋል፡፡
"የኢትዮጵያን ክብር አሳልፎ የሚሰጥ ትውልድ የለም" ያሉት ወጣቶቹ፤ አሜሪካም ሆነ የአውሮፓ ህብረት እንዲሁም ሌሎች ሀገራት ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው የዘመናት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲቀጥልም እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡