ወጣቶች ሀገራቸውን ላለማስደፈር በጋራ ቆመው መታገል ይገባቸዋል-- ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቶች ሀገራቸውን ላለማስደፈር በጋራ ቆመው መታገል ይገባቸዋል-- ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ
ግንቦት 22/2013 (ኢዜአ) "ኢትዮጵያውያን ጥንትም ሆነ ዛሬ፣ በእናት ሀገራቸው ጉዳይ፣ ብሔራዊ ጥቅማቸው እና በውጭ ኃይሎች ጥቃት አንድም ጊዜ ተለያይተው አያውቁም ሲሉ " ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ አስታወቁ።
ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደው "ድምጻችን ለነጻነታችን እና ሉዓላዊነታችን"በሚል የወጪ ሀይሎችን ጣልቃገብነት ለመቃወም እና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 2ኛ ዙር የውሃ ሙሌት የድጋፍ ሰልፍ መልዕክት አስተላልፈዋል ።
ኢትዮጵያ በዓለም የጥቁር ህዝቦች ታሪክ፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገር አኩሪ ታሪክ ካለቸው ሀገራት መካከል ደምቃና ከፍ ብላ፣ በታሪክ ድርሳናት ተመዝግባ የምትገኝ የሁላችንም የኩራት ምንጭ ናት ያሉት ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በዘመናት የገጠማትን ወረራና ጥቃት አንድም ግዜ ብሔራዊ ክብሯና ሉያላዊነቷን ሳታስደፍር፣ በጀግናና በቁርጥ ቀን ልጆቿ ድል ስትቀናጅ ቆይታለች ብለዋል ፡፡
ለዚህ ደግሞ በአድዋ፣ በካራማራ እና በተለያዩ አውደ ግንባሮች፣ በመስዋዕትነት ደምቆ የተፃፈው የአልገዛም ባይነት አኩሪ ታሪካችን ህያው ምስክር ነው ብለዋል ፡፡
ኢትዮጵያ በተለያየ ግዜ በውጪ ኃይሎች የተደረገባትን ጣልቃ ገብነት መሪዎቿ እንኳን ቢቀያየሩም፣ በሀገራቸው ጉዳይ ፍፁም የማይደራደሩና ህይወታቸውን ገብረው ታሪካቸውን እያደሱ የሚቀጥሉ መሆናቸውን እያሳዩ መቆታቸውን ገልጸው፣ አሁንም እያሳዩ ይገኛሉ፤እኛም የእነሱ ልጆች ነን ሲሉ ገልጸዋል ።
ኢትዮጵያውያን ጥንትም ሆነ ዛሬ፣ በእናት ሀገራቸው ጉዳይ፣ ብሔራዊ ጥቅሞቿና በውጭ ኃይሎች ጥቃት፣ አንድም ግዜ ተለያይተው አያውቁም! ሀገራችን አኩሪ የድል ታሪክ ያላት ብትሆንም፣ አብዛኛው ህዝቦቿ በድህነት እና በመሰረተ ልማት መጓደል ውስጥ እየኖሩ ይገኛሉ ብለዋል ምክትል ከንቲባዋ።
ይህንን ሁኔታ ለመቀየር ያላትን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት፣ ፍትሃዊ በሆነ አግባብ ለመጠቀም፣ ሌት ተቀን እየታተረች በለውጥ ጎዳና ውስጥ ትገኛለች ያሉት ወ/ሮ አዳነች እኛ ኢትዮጵያውያን ማንንም ለመጉዳትና ለመበደል እንደማንሻ ሁሉ፣ ማንም እንዲጎዳንና እንዲበድለን የማንፈልግ ህዝቦች ነን ብለዋል ።
ይሁን እንጅ፣ የማደግ ህልማችን እንዲጨናገፍ የውጭ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ከውስጥ ባንዳዎች ጋር በመቀናጀት፣ ከድህነት የመውጣት ጉዟችንን ለማደናቀፍ ከተቻላቸውም ለማስቆምና ህዝባችንን ለልመናና ለረሃብ ለመዳረግ ቀን ከለሊት እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል ፡፡
በተለይም በራሳችን ገንዘብና ጉልበት የምንገነባው የታለቁ የህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ሙሌት ተጠናቆ፣ ለህዝቡ ራት እና መብራት እንዳይሆን ያልፈነቀሉት ድንጋይ፣ ያልሸረቡት ሴራ የለም ያሉት ምክትል ከንቲባዋ ፤እኛ ግን ምንም እንኳን አብዛኛው የውሃ ድርሻ የኛ ቢሆንም፣ በፍትሃዊነት እንጅ ሌሎችን ጎድቶ የመጠቀም ሃሳብ እና ድርጊት እንደሌለ ራሳቸው ከሳሾችም ጭምር ያውቁታል ብለዋል ፡፡
በመሆኑም ዛሬም ሆነ ወደፊት፣ አባይን በፍትሃዊነት የመጠቀም መብት በፍፁም ሌሎችን እንዲጎዳ አንፈልግም ፤የመጠቀም መብታችንን ከማረጋገጥ ወደ ኋላ አንልም ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያ የውስጣዊ ሠላም ማስጠበቅ በዋነኝነት የህዝቧና የመንግስቷ መሆኑ ግልፅ ነው ያሉት ከንቲባዋ ፤ አሸባሪው የህውሃት ጁንታ ቡድን የሀገርን ክብርና ኩራት በሆነው መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት የፈፀመ ሲሆን፣ በማይካድራ ንፁሃን ላይ ጭፍጨፋ ከማድረጉም በላይ፣ በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች የዘር ማጥፋት ዘመቻ እንዲካሄድ መሪ ተዋናይ ሆኖ ተንቀሳቅሷል፤ ፈፅሟል፤ አስፈፅሟል ብለዋል ወ/ሮ አዳነች አቤቤ።
ይህ ኃይል ከጥፋቱ እንዲታቀብ መንግስት ያካሄደውን የሠላም ማስከበር እርምጃ ውጤታማ ብቻ ሳይሆን ፍትሃዊም ነው ብለዋል፡፡
ይህንን በሽበርተኝነት ላይ ለተሰማራ ሃይል ማስወገድ አለማቀፋዊ ድጋፍ የሚሠጠው እንጅ፣ በምንም መመዘኛ የሚነቀፍና የሚወገዝ ሊሆን አይችልም ነው ያሉት፡፡
ነገር ግን አሜሪካና አጋሮቿ የዚህ ኃይል የጥፋት ጉዞና ተግባር ሳይረዱ፣ በውስጣዊ ጉዳይ ጭምር በመግባት የሚያስቀምጡት ቅድመ ሁኔታና የጉዞ ማዕቀብ በፍፁም ተቀባይነት የሌለው ብቻ ሳይሆን፣ ቆም ብለው በማስተዋል ሊያርሙትና ሊያስተካክሉት የሚገባ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
በመሆኑም የኛ የውስጥ ጉዳይ የኛ ብቻ እንጂ፣ የማንንም ጣልቃ ገብነት የማይሻ በመሆኑ ከዚህም የዘለለ ጣልቃ ገብነት ሉዓላዊነትን መድፈር መሆኑ ጭምር ሊታወቅ እንደሚገባም አመልክተዋል ።
ጠላቶቻችን የሚመኟት የተዳከመች ሃገር እንደማትኖር ያላችሁን ቁርጠኝነት፣ ተነሳሽነት፣ ከአባቶቻችን በወረሳችሁት የአርበኝነትና አልደፈርባይነት ወኔን አጎልብታችሁ፣ የውስጥ ባንዳዎችንና የውጭ ታሪካዊ ጠላቶቻችንን ሴራ በማክሸፍ የዘመናችሁን አድዋ በደማቅ ብዕር እንደምትከትቡ አንጠራጠርም ብለዋል ።
ብሄራዊ ምርጫችን እነሱ ሲፈቅዱልን የምናካሂደው፣ ሳይፈቅዱ የምንተወው ሳይሆን፣ የራሳችን የውስጥ ጉዳይ በመሆኑ፣ ይልቁንም ምርጫው ሠላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ዘርፈ ብዙ ተሳትፏችሁን አጠናክሩ።
በዚህም የምትወዷት ሃገራችሁን በታሪክ አሸናፊ የምትሆንበት፤ እናንተም ካርዳችሁን እንጂ ህይወታችሁን የማትሰጡበት እንዲሆን ማድረግ ይገባችኋል፡፡
በመጨረሻም እያንዳንዳችን በመካከላችን ያለውን ጥቃቅን ልዩነቶች እና ጥርጣሬዎችን ከውስጣችን አስወግደን፣ ዋናው መዋጊያ መሳሪያችን ኢትዮጵያዊ አንደነታችን መሆኑን ተረድተን፣ ይህን ወሳኝ ምዕራፍ በድል በመሻገር የኢትዮጵያን ታላቅነት የምናስቀጥል ትውልድ መሆናችን ለአለም እናስመስክር ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል ።