ቀጥታ፡

የሼህ ሆጀሌ ቤተ-መንግስት ታሪካዊ ቅርስነቱን ሳይለቅ በማልማት እንዲጠበቅ ይደረጋል - ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ግንቦት 22/2013 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ የሚገኘው የሼህ ሆጀሌ ቤተ-መንግስት መስህብነቱና ታሪካዊ ቅርስነቱን ሳይለቅ እንዲለማና እንዲጠበቅ ይደረጋል ሲሉ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ምክትል ከንቲባዋ ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሃሰን እና ከአዲስ አበባ አስተዳደር  ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን የሼህ ሆጀሌን ቤተ-መንግስት ጎብኝተዋል።

ሼህ ሆጀሌ በ1880ዎቹ አካባቢ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ገዢ ከነበሩና በወቅቱ ታዋቂ ከነበሩ የጠቅላይ ግዛት አስተዳዳሪዎች አንዱ እንደነበሩ የታሪክ ድርሳናትያስረዳሉ።

በወቅቱ ሼህ ሆጀሌ የሚያርፉበትና ቤተሰቦቻቸውንም የሚያኖሩበት የከተማ ቦታ አዲስ አበባ ውስጥ በአጼ ምኒልክ ተሰጥቷቸው እንደነበርም እንዲሁ። 

የሼህ ሆጀሌ ቤተ-መንግስት በዘመኑ በአዲስ አበባ ከሚገኙ ጥንታዊና መዲናዋን እንደ ስሟ ካዘመኗት ህንጻዎች አንዱ መሆኑን ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል።

በጉለሌ ክፍለ ከተማ የሚገኘው ይህ ጥንታዊ ቤተ-መንግስት የአዲስ አበባን ነዋሪዎችና የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ሕዝቦችን ጥንታዊ መስተጋብር የሚያጎላ እንደሆነም ገልጸዋል።

ለመዲናዋ የሥልጣኔ አሻራውን ያኖረውና ውበትን ያጎናጸፈው ይህ ቤተ መንግስት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው እምብዛም በነበረበት ወቅትም በንግድ እንቅስቃሴ ለከተማዋ መነቃቃት መፍጠሩን አውስተዋል።

በቅርስነት የተመዘገበውን ቤተ-መንግስት ጠቀሜታ አጉልቶ ለማሳየት እድሳትና ልማት የግድ በመሆኑ ከተማ አስተዳደሩ ለያዘው እቅድ የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ምክትል ከንቲባዋ ጠይቀዋል።

የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው፤ አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን መሆኗን በርካታ ማሳያዎች እንዳሏት ተናግረዋል።

የሼህ ሆጀሌ ቤተ-መንግስትም የቤኒሻንጉል ሕዝቦች በከተማዋ የእኔነት ስሜት ኖሯቸው ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በጥልቅ ቁርኝት ለዘመናት እንዲኖሩ ማድረጉን ገልጸዋል።

የስፍራው የአዲስ አበባ እና የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልልን የጋራ ልማት የሚጠይቅ በመሆኑ ክልሉ የራሱን አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

እድሳቱ እንዲከናወን በቤተ-መንግስቱ ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች ተለዋጭ ቤት እንዲያገኙ ለማድረግ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በቅርበት እንደሚሰሩም አክለዋል።

ጎብኚዎቹ የስራ ሃላፊዎች በቤተ-መንግስቱ ቅጥር ግቢ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አከናውነዋል።

ሼህ ሆጀሌ በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግስት በአድዋ ጦርነት 5 ሺህ ወታደሮችና ፈረሰኞችን በማሰለፍ ለድሉ አስተዋጽኦ ማድረጋቸው በታሪክ ሰፍሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም