የውጭ ሀገራት ጣልቃ ገብነትን በመቃወም የሚካሄደው ሰልፍ የታለመትን ግብ እንዲያሳካ ወጣቶች ሊተባበሩ ይገባል - የወጣቶች ማህበር - ኢዜአ አማርኛ
የውጭ ሀገራት ጣልቃ ገብነትን በመቃወም የሚካሄደው ሰልፍ የታለመትን ግብ እንዲያሳካ ወጣቶች ሊተባበሩ ይገባል - የወጣቶች ማህበር
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ላይ የሚስተዋለውን የውጭ ሀገራት ጣልቃ ገብነት በመቃወም የሚካሄደው ሰልፍ የታለመትን ግብ እንዲያሳካ ወጣቶች ሊተባበሩ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር አሳሰበ።
የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር "ድምጻችን ለነጻነታችንና ሉዓላዊነታችን" በሚል በሚካሄደውን አገር አቀፍ ሰልፍ በመዲናዋ የሚካሄደውን መርሃ ግብር አስመልክቶ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥቷል።
የሰልፉ ዓላማ ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጫና መቆም አለበት በሚል ጽምጻችንን ማሰማት ነው ሲሉ የማህበሩ ፕሬዝዳንት ገዛኸኝ ገብረማርያም ገልጿል።
ኢትዮጵያ ጠንካራ አገር መሆኗን ህዝቦችዋም በአገራቸው ጉዳይ አንድ መሆናቸው፣ ኢትዮጵያና ሰላም ወዳድና ከጎረቤት አጋሮች ጋር አብሮ መልማትን የምታስቀድም አገር መሆኗን የሚያንጸባርቁ መልዕክቶች በሰልፉ ላይ ይተላለፋሉ ብሏል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያውያን የሕልውና ጉዳይ መሆኑንና ወጣቱ አገሩን በመጠበቅ የበኩሉን ሃላፊነት መወጣት እንዳለበትም በሰልፉ ላይ ይገለጻል ነው ያለው።
መርሃ ግብሩ የታለመትን ግብ እንዲያሳካ ወጣቶች ሊተባበሩና በጋራ ድምፃቸውን ሊያሰሙ ይገባል ብሏል።
ሰልፉ አገራዊ ፍቅርና አንድነት የሚገለጽበት በመሆኑ ከሰልፉ ዓላማ ውጪ ሌሎች መልዕክቶችን ማስተላለፍ የተከለከለ መሆኑንም የማህበሩ ፕሬዝዳንት ጠቅሷል።
ሰልፉ ነገ ማለዳ ከ12 ሰዓት ጀምሮ በአዲስ አበባ ስታዲየምና አካባቢው እንደሚካሄድና ወጣቶች ሰልፉ የታለመለትን ዓላማ አሳክቶ በሰላም እንዲጠናቀቅ የድርሻቸውን መወጣት አለባቸው ብሏል።
ለሰልፉ ስኬትና ሰላማዊነት ማህበሩ ከጸጥታ ሃይሉና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ የሚሰራ መሆኑንም አረጋግጧል።
"ድምጻችን ለነጻነታችንና ሉዓላዊነታችን" በሚል በመዲናዋ የሚካሄደው ሰልፍ በሰላም እንዲከናወን የአዲስ አበባ ህዝብ የተለመደውን ትብብር እንዲያደርግም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጠይቋል።
በኢትዮጵያ ላይ የሚስተዋለውን የውጭ ሀገራት ጣልቃ ገብነት በመቃወም በሀገር አቀፍ ደረጃ 1 ሚሊዮን ወጣቶች የሚሳተፉ ሲሆን ከዚህ ውስጥ በአዲስ አበባ 100 ሺህ ወጣቶች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።