ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነት ማንም ሊያፈርሰውና ወደኋላ ሊመልሰው የሚችለው ጉዳይ አይደለም - አቶ ሽመልስ አብዲሳ

ግንቦት 21 /2013 (ኢዜአ) "የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነት ማንም ሊያፈርሰውና ወደኋላ ሊመልሰው የሚችለው ጉዳይ አይደለም" ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ ገለፁ።

በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ወጪ በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን እነሞርና ኤነር ወረዳ ለሚገነባው ጉሰባጆይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ እና የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳው የመሰረተ ድንጋይ ዛሬ አኑረዋል።

አቶ ሽመልስ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር "የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነት የነበረ፣ አሁንም ያለና ወደፊትም የሚቀጥል ነዉ" ብለዋል።

በቋንቋ፣ በባህልና በተለያዩ ጉዳዮች መለያየት ቢኖርም ከፍተኛ የሆነ የህዝብ ትስስር መኖሩን ገልፀው፤ "ኢትዮጵያዊነታችን በብዙ ነገር የተጋመደና የተሳሰረ በምንም ዓይነት ሁኔታ ሊበጠስ የማይችል ነው" ብለዋል።

ብዙዎች ይህንን መተሳሰር ለመበጠስ ሞክረው እንዳልተሳካላቸው አስታውሰው፤ ኢትዮጵያ የተዳከመች እየመሰላቸው የማይሆን ነገር እንደሚሞክሩ ገልፀዋል።

"ኢትዮጵያ ላይ የማይሆን ነገር የሞከሩ ሁሉ ጠፍተዋል" ያሉት አቶ ሽመልስ፤ የኢትዮጵያ አንድነት፣ ሰላም፣ ልማትና ብልፅግና እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

"የገፉን ሁሉ አንዳንዶቹ ይቅርታ ይጠይቁናል፤ አንዳንዶቹ በዚያው ይጠፋሉ፤ ኢትዮጵያ ትቀጥላለች" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም