የስራ እድል በመፍጠርና ሃብት በማፍራት ኢትዮጵያን ከውጭ ጥገኝነት ማላቀቅ አለብን- ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
የስራ እድል በመፍጠርና ሃብት በማፍራት ኢትዮጵያን ከውጭ ጥገኝነት ማላቀቅ አለብን- ወጣቶች
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21/2013/ኢዜአ/ ኢትዮጵያ ያላትን ሃብት በመጠቀምና ሥራ በመፍጠር ከውጭ ጥገኝነት ጣልቃ ገብነት ለማላቀቅ በትብብር መስራት አለብን ሲሉ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች ገለጹ።
ለኢዜአ አስተያየቷን የሰጠችው የሄለን ቡና መስራች ወጣት ቤተልሄም ሥዩም ኢትዮጵያዊያን ከተባበርንና ሀገርን ከሚጎዳ አስተሳሰብ ከተላቀቅን ውጤታማ መሆን እንችላለን ትላለች።
በተለይ ወጣቶች ጉልበታቸውንና እውቀታቸውን ሀገርና ህዝብ በሚጠቅም ተግባር ላይ ማዋል አለባቸው ነው ያለችው።
የጥበብ ስራዎችን ማቅረብና የጥበብ አድናቂዎችን ጥበበኞችን የሚያገናኘው ናይል ስትሪም የተሰኘ ድረገፅ መስራች ወጣት በቃሉ ተመስገን፤ በዚህ ዘመን በተለይ ወጣቶች ሳይንስና ቴክኖሎጂን በስፋት በመጠቀም ሀገራቸውን ለማሳደግ መስራት አለባቸው ብሏል።
በሁሉም መስኮች የሥራ ፈጣሪዎች ከተበራከቱ የኢትዮጵያ መፃኢ አደል ተስፋ የሚጣልበትና ለውጥ የሚመዘገብበት እንደሚሆን ያምናል።
በመሆኑም ወጣቶች በተነሳሽነትና በፈጠራ አገር የሚቀይሩ ሥራዎችን በትብብር ማከናወን አለባቸው፤ ይህ ሲሆን ኢትዮጵያ ከጥገኝነትና ከውጭ አገራት ጫና መላቀቋ ግድ ይሆናል ብሏል።
የትርፍ ሰዓት ሥራ ፈላጊዎችንና ቀጣሪ ድርጅቶችን የሚያገናኝ ድረ-ገፅ መስራች የሆነችው ቤዛዊት አድማሱም ሥራ ፈጣሪዎችን በማበራከትና ሀብት በማፍራት ገቢ ማሳደግ ከተቻለ ኢትዮጵያ አድጋ ከሌሎች አገራት ከጥገኝነት መላቀቅ ትችላለች ነው ያለችው።
ኢትዮጵያዊያን ከመከፋፈል፣ ግጭት፣ አለመግባባት ወጥተን አገራችንን እንታደግ ሲሉም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ2 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ዜጎች የሥራ እድል የተፈጠረላቸው መሆኑን ከፌዴራል የስራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።