የአዋሽ ነዳጅ ማከማቻን ከባቡር ሃዲድ ጋር የሚያገናኘውና የነዳጅ ማራገፊያ መሰረተ ልማት ግንባታ ስራ እየተፋጠነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአዋሽ ነዳጅ ማከማቻን ከባቡር ሃዲድ ጋር የሚያገናኘውና የነዳጅ ማራገፊያ መሰረተ ልማት ግንባታ ስራ እየተፋጠነ ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21/2013/ኢዜአ/ የአዋሽ ነዳጅ ማከማቻን ከባቡር ሃዲድ ጋር የሚያገናኘውና የነዳጅ ማራገፊያ መሰረተ ልማት ግንባታን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ በፍጥነት እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ገለጸ።
የትራንስፖርት ሚኒስቴር በሥሩ ያሉ ተጠሪ ተቋማት እያከናወኑ ያሉትን የመንገድ፣ የባቡር፣ የደረቅ ወደብ አገልግሎት እና ሌሎች የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች አስጎብኝቷል።
በጉብኝቱም የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን፣ የኢትዮ-ጅቡቲ ቡመስመር፣ የኢትዮጵያ ክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ፣ የሞጆ ደረቅ ወደብና ተርሚናል፣ የቢሾፍቱ፤ ጨፌ ዶንሳ ሰንዳፋ መንገድ እና እና የአዋሽ ነዳጅ ማቆሪያና ማራገፊያ ፕሮጀክት ግንባታ ሂደት ተጎብኝቷል።
የአዋሽ ነዳጅ ማቆሪያን ከባቡር ሃዲድ ማገናኘት እና የነዳጅ ማራገፊያ መሰረተ ልማት ግንባታ በመገናኛ ብዙሃን ተጎብኝቷል።
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የባቡር ኔትዋርክ ዘርፍ ምክትል ስራ አስፈፃሚ አቶ በሐይሉ ስንታየሁ እንደገለጹት ኮርፖሬሽኑ የአዲስ አበባን ቀላል ባቡርና የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስርመር ግንባታ ወደ ስራ ማስገባቱን ገልፀው የአገሪቷን የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ የበኩሉን አስተዋፅዖ እየተወጣ ይገኛልም ብለዋል።
የአዋሽ ኮምቦልቻ ሃራ ገበያ የባቡር መስመር ዝርጋታን አጠናቆ ወደ ስራ ለማስገባት በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በ2013 በጀት አመት ኮርፖሬሽኑ የአዋሽ ነዳጅ ማቆሪያን ከባቡር ሃዲድ ማያያዣ እና የነዳጅ ማራገፊያ መሰረተ ልማት ግንባታ ለማከናወን አቅዶ ወደ ተግባር መግባቱን ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱም የኢትዮ ጁቡቲ መስመር በአዋሽ ከተማ ከሚገኘው የነዳጅ ማጠራቀሚያ ጋር ማገናኘት፣ የአዋሽ ኮምቦልቻ ሃራ ገበያ መስመር ከኢትዮ-ጅቡቲ ጋር ማገናኘት፣ የፍሳሽ ጭነት ማራገፊያ ቦታ መገንባት እና መተላለፊያ ፌርማታ መገንባት መሆኑን ጠቅሰዋል።
ለፕሮጀክቱ ግንባታ ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚደረግ ሲሆን 5 ነጥብ 1 ኪ.ሜ ርዝመት እንዳለው ተጠቁሟል።
በጥር 23 ቀን 2013 በይፋ የተጀመረ ሲሆን በታህሳስ 10 ቀን 2014 ዓ.ም ለማጠናቀቅ ዕቅድ ተይዟል ብለዋል።
የኢትዮ-ጅቡቲ ስታንዳርድ ጌጅ አክሲዮን ማህበርን የስራ እንቅስቃሴም በተመለከተ ማህበሩ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ዕቃ የማመላለስ አቅሙ ከ20 እሰከ 30 በመቶ ጭማሪ እያሳየ መምጣቱን ተገልጿል።
የኢትዮ-ጅቡቲ ስታንዳርድ ጌጅ አክሲዮን ማህበር ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ጥላሁን ሳርካ፤ አክሲዮን ማህበሩ የገቢና ከወጭ ንግድ አገልግሎት ጎን ለጎን ለመንገደኞች የትራንስፖርት አገልገሎት በመስጠት ላይ መሆኑን ገልፀዋል።
በአጠቃላይ ባለፉት ሶስት አመታት አክሲዩን ማህበሩ ውጤታማ ስራ ማከናወኑንም አብራርተዋል።
የቢሾፍቱ-ጨፌ ዶንሳ-ሰንዳፋ የመንገድ ግንባታ ፕሮክትም የተጎበኘ ሲሆን አሁን ላይ ግንባታው 19 በመቶ መድረሱን የፕሮጀክቱ ኃላፊ ኢንጅነር አለማየሁ በቀለ ተናግረዋል።
ግንባታው ከተጀመረ 1 ዓመት ከአራት ወር ማስቆጠሩን ተናግረው በቀጣይ አመት አስፓልት የማንጠፍ ስራ እንደሚከናወን ገልፀዋል።
አካባቢው ከፍተኛ የሆነ የግብርና ምርት ያለበት በመሆኑ አርሶ አደሩ ምርቱን ለገበያ ለማቅረብ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተገልጿል።