ቀጥታ፡

“ድምፃችን ለነፃነታችን” በሚል በመላው ሀገሪቱ ሰላማዊ ሠልፍ ሊካሄድ ነው

አዲስ  አበባ ፣ግንቦት 21 ቀን 2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ላይ የሚስተዋለውን የውጭ ሀገራት ጣልቃ ገብነት በመቃወም 1 ሚሊዮን ወጣቶች የሚሳተፉበት ሀገር አቀፍ ሰልፍ ነገ ይካሄዳል።

ሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ነገ የሚካሄደውን ሰልፍ በማስመልከት መግለጫ ሰጥቷል።

የሚኒስቴሩ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አድነው አበራ በሰጡት መግለጫ በኢትዮጵያ ላይ የሚስተዋለውን የውጭ ሀገራት ጣልቃ ገብነት በመቃወም 1 ሚሊዮን ወጣቶች የሚሳተፉበት ሀገር አቀፍ ሰልፍ በነገው እለት ከማለዳው 12፡00 ሰዓት ጀምሮ ይካሄዳል።

የአገሪቱን ሉአላዊነት የሚፈታተኑ ተግባራት በተለያዩ የውስጥ እና የውጭ ሃይሎች አሉታዊ ተጽእኖ ለመፍጠር እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን በመግለጫቸው አብራርተዋል።

እነዚህ አካላት ኢትዮጵያን ከያዘችው የልማትና ብልፅግና ጉዞ ለማደናቀፍ በጥረት ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

በመሆኑም ይህንን እኩይ አላማና ጣልቃ ገብነት የሚያወግዝ ሰልፍ በሀገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች ነገ ከማለዳው ጀምሮ ይካሄዳል ብለዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብና ሌሎች በትላልቅ ፕሮጀክቶች ላይ ማተኮር እንዲሁም 6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ነጻ፣ ፍትሃዊ፣ ተአማኒና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የሁላችንም ጥረት ያስፈልጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ባህል በማዘመን የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ የተያዙ እቅዶች እንዲሳኩ ለማስቻልም እንዲሁ።

የውጭ አገራት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዮች ላይ እያደረጉት ያሉት አግባብነት የሌለው ጣልቃ ገብነትና የመከፋፈል እሳቤ በጋራ ቆመን ማውገዝ ይገባናል ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

በሚኒስቴሩ የወጣቶች ተሳትፎ ንቅናቄና ማካተት ዳይሬክተር ማቲዮስ አሰፋ፤ ኢትዮጵያ ከአሜሪካም ሆነ ከሌሎቹ ምዕራባውያን ሀገራት ለበርካታ አመታት የዘለቀ መልካም ግንኙነት አላት ብለዋል።  

ከሰሞኑ የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ላይ የጉዞ ገደብ መጣሉ ተገቢነት የሌለውና ሃላፊነት የጎደለው መሆኑን አብራርተዋል።

ከአንድ የዴሞክራሲ ተምሳሌት ከሆነች አገር የማይጠበቅ እና የሁለቱን አገራት የረዥም ጊዜ መልካም ግንኙነትና አብሮነት ያላገናዘበ መሆኑንም ገልጸዋል።

በነገው እለት የሚደረገው ሰልፍ በሁሉም ከተማ አስተዳደሮች እና በዋና ዋና ከተሞች ከማለዳው ጀምሮ በተመሳሳይ ሰዓት የሚከናወን መሆኑ ታውቋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ በድምሩ ከ1 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም