ቀጥታ፡

የዘንድሮው የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ነገ ይጠናቀቃል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21/2013/ኢዜአ/ የዘንድሮው የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ነገ ፍጻሜውን ያገኛል።

የዘንድሮው ፕሪሚየር ሊግ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን መመሪያ ታሳቢ በማድረግ በባህርዳር፣ ሐዋሳ፣ ድሬዳዋና አዲስ አበባ ከተሞች ሲካሄድ ቆይቷል።

ከግንቦት 17 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ከ16ኛ እስከ 18ኛ ሳምንት የሊጉ የማጠቃላያ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም በመካሄድ ላይ ሲሆን ውድድሩ ነገ ይጠናቀቃል።

በዚሁ መሰረት በ18ኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታዎች ቀድሞ የሊጉ አሸናፊ መሆኑን ያረጋገጠው ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ነገ ከመከላከያ ጋር ከጠዋቱ 3 ሰዓት ላይ ጨዋታውን ያደርጋል።

በ28 ነጥብ የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ እየመራ የሚገኘው ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በ24 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው መከላከያ የሚያደርጉት ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የሊጉ አሸናፊ የሆነው ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን በ2010 ዓ.ም የውድድሩ አሸናፊ እንደነበር የሚታወስ ነው።

መከላከያ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ በ2009 ዓ.ም ሲጀመር የመጀመሪያው የውድድሩ አሸናፊ ክለብ ነበር።

ዛሬ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም በተደረገ 18ኛ ሳምንት ጨዋታ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ፌደራል ፖሊስን 17 ለ 16 አሸንፏል።

ውጤቱንም ተከትሎ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በ24 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን የያዘ ሲሆን ፌደራል ፖሊስ ደግሞ በ22 ነጥብ በውድድሩ ዓመቱ አራተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።

የ2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የክለቦች ተሳትፎ በታሰበው መልኩ የሄደበት ነው ማለት አይቻልም።

በትግራይ ክልል በነበረው ችግር የመቐለ ሰብዓ እንደርታ የእጅ ኳስ ክለብ በውድድሩ ላይ ያልተሳተፈ ሲሆን የቡታጅራ ከተማ የእጅ ኳስ ክለብ ደግሞ "የበጀት ችግር አጋጠመኝ" በማለቱ ሳይወዳደር ቀርቷል።

በመጀመሪያ ዙር የሊጉ ውድድር ተሳትፎ ያደረገው ጎንደር ከተማም "የበጀት እጥረት አጋጥሞኛል" በሚል በሁለተኛው ዙር ራሱን ከውድድር ውጪ ማድረጉ የሚታወስ ነው።

ባህርዳር ከተማ ዘንድሮ ሊጉን የተቀላቀለ አዲስ ክለብ ሲሆን በዘጠኝ ክለቦች የተጀመረው ፕሪሚየር ሊግ በስምንት ክለቦች ተሳትፎ ተጠናቋል።

በ2012 ዓ.ም ፕሪሚየር ሊጉን የተቀላቀለው ሚዛን አማን ከተማ በዘንድሮው ውድድር አንድም ጨዋታ ሳያሸንፍ የመጨረሻውን ደረጃ ይዞ አጠናቋል።

ነገ በሚካሄደው የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የመዝጊያ ስነ ስርዓት ከአንድ እስከ ሶስት ለወጡ ክለቦች የዋንጫና የሜዳሊያ ሽልማት ይበረከታል።

በተጨማሪም ለኮከብ ተጫዋች፣ ለኮከብ አሰልጣኝና ለኮከብ ዳኛ ልዩ የዋንጫ ሽልማት የሚሰጥ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ የስፖርት ኮሚሽንና የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም የእጅ ኳስ ክለቦች አመራሮች በማጠቃለያ ስነ ስርዓቱ ላይ ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የ2012 ዓ.ም የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የተቋረጠ ሲሆን ውድድሩም ያለ አሸናፊ እንዲሰረዝ መደረጉ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም