ኢትዮጵያውያን እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ እንደ አንድ ልብ መስካሪ ሆነው መቆም አለባቸው - የብልፅግና ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያውያን እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ እንደ አንድ ልብ መስካሪ ሆነው መቆም አለባቸው - የብልፅግና ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
ግንብት 20 /2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያውያን እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ እንደ አንድ ልብ መስካሪ ሆነው መቆም አለባቸው ሲል የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ጥሪ አቀረበ።የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሀገራዊና ጂኦ ፖሊቲካዊ ጉዳች ላይ በመምከር መልዕክት እስተላልፏል።
ፓርቲው በመልዕክቱ ጅማሬም ኢትዮጵያ የምትገኝበት ጂኦ ፖሊቲካዊ አካባቢ ዛሬም እንደትናንቱ የዓለም የአይን ማረፊያ ሆኖ ይገኛል።
ከሜዲትራኒያን ባህር ቀጥሎ ልዩ ልዩ የንግድ እንቅስቃሴዎች የሚደረግበት የዓለም የንግድ እንቅስቃሴ መሆኑ ይጠቀሳል ነው ያለው።
በዚህ ቀጠና ላይ የበላይነት መያዝ በዓለም ዓቀፍ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ይታመናል ብሏል ስራ አስፈጻሚው።
በዚሁ ምክንምያት ብዙ ሀገራት ከሌላ ዓለም ዳርቻ መጥተው በቀይ ባህር ዳርቻ የጦር መንደሮችን የመመስረትና ወደቦችን የማልማትና የንግድ መስመሮችን ከመዘርጋት ባለፈ በቀጣናው ፖለቲካ ላይ እጃቸውን ከማስገባት ተቆጥበው አያውቁም።
ኢትዮጵያ ደግሞ ከጥንት ጀምሮ በቀይ ባህር ሲደረግ በነበረው ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊና የንግድ እንቅስቃሴ ጉልህ ሚና ነበራት።
ከሌሎች ሀገራት ባለፈ ለቀይ ባህር ካላት ቅርበት አንጻር ብትፈልግ እንኳን ከፖለቲካ ጫናው ማምለጥ አትችልም።
በመሆኑም አንዳንድ አካላት በቀይ ባህር ላይ ያላቸው ፖለቲካዊ ፍላጎት የሚሳካ የሚመስላቸው ኢትዮጵያ ስትዳከም ነው።
በዚህ ደግሞ እንደ ሉዓላዊ አገር ፍጹም ተቀባይነት የሌለውና የአገሪቷን ጥቅም በሀይል ወይም በዲፕሎማሲ ተጽእኖ የማጣት ምንም አይነት ፍላጎት እንደሌለ መታወቅ አለበት።
ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር ጥቅም ለማግኘት ሲታሰብም ከጎረቤት ሀገራት ጋር በሰጥቶ መቀበል መርህ እንጂ ከማንም ጋር እሰጣገባ ውስጥ በመግባት አይደለም ብሏል በመግለጫው።
የእስካሁንም የዲፕሎማሲ ታሪክ ማሳያ ሊሆን የሚችል መሆኑንና ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር አካባቢ ካላት ጂኦ ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ባለፈ የአባይ ዋና ምንጭ በመሆኗ የአፍሪካን ቀንድና የሰሜን ምስራቅ አፍሪካን ሁኔታ የመወሰን አቅም አላት።
ከግሪክ ስልጣኔ ጀምሮ ግሪካውያንና አውሮፓውያን ኢትዮጵያን ለማግኘት ከተጉበት ምክንያት አንዱ የአባይን ምንጭ ለማወቅና ለመቆጣጠር እንደሆነ የታሪክ ማዛግብት ያስረዳሉ።
በነዚህ ምክንያቶች ኢትዮጵያ እየጠነከረች ከመጣች ጥቅማቸው የሚነካ የሚመስላቸው አካላት ስጋት ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉ ግልጽ ነው።
ሆኖም አንድ መታወቅ ያለበት ሃቅ ኢትዮጵያ ዱሮም ሆነ ዛሬ የሌሎች ጥቅም ላይ ተጽእኖ የመፍጠር ዓላማ የላትም።
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ጥቅም ላይም ሌሎች ተጽእኖ እንዲፈጥሩ ማንም አይሻም፤ ለውጡን ተከትሎም በቀጣናው የተረጋጋ ሁኔታ እንዲፈጠር የተሰሩ ስራዎች አሉ።
ከኤርትራ ጋር ያለው ግንኙነት መታደሱና አጠቃላይ በቀጣናው የተፈጠረው ትስስር ቀናውን ለሚይታዘቡ አካላት ደስ የሚያሰኛቸው አልሆነም።
በቅረቡም ከሱዳን ጋር የተገባበት ሁኔታ ከአገሪቷ ጋር ከነበረው የረጅም ዘመናት ግንኙነት አኳያ ሲፈተሽ ፈጽሞ መፈጠር አልነበረበትም ብሏል።
አሁንም ያንኑ ግንኙነት ታሳቢ በማድረግ በድንበር አካባቢ የተፈጠረውን ችግር በሰላማዊ ሁኔታ ለመፍታት ይሰራል።
ሱዳኖችም ከመስፋፋትና ከጠብ ጫሪነት ወጥተው በሰላማዊ መፍትሄ እንደሚቆሙ ተስፋ አለን ብሏል ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው።
የኢትዮጵያን ስልጣኔ የማይሹ አካላት ዋና አላማ ደካማ ኢትዮጵያን መፍጠር ሲሆን ለዚህ ደግሞ ሶስት መንገዶችን የሚጠቀሙ ሲሆን አንዱ ከጎረቤቶቿ ጋር ወደ ጦርነት ማስገባት ነው።
ሌላው የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ማዳከምና ኢትዮጵያውያንን በአካባቢና በእምነት ማጋጨት ሌላ የሚጠቀሙት ስልታቸው ነው።
ከጥንት ጀምሮ ኢትዮጵያ በሺዎች የሚቆጠሩ ጦርነቶችን ከወራሪዎች ጋር አድርጋለች፤ ጦርነቶቹ ዋና አለማም አገሪቷ ፋታ አገኝታ የስልጣኔ መንገድ እንዳትከተል ማድረግ ነው።
ይህም የባህር በር ከማሳጣት ጀምሮ ዓለም አቀፍ ብድርና እርዳታ እንዳታገኝ ከማድረግና ታላላቅ ፕሮጀክቶችን እንዳታካሄድ አግዷታል።
የአባይ ግድብንም ሆነ ሌሎች ግድቦችን ለመገንባት የተደረጉ ጥረቶች ያልተሳኩት በዚሁ ምክንያት እንደነበረም በመግለጫው ተመላክቷል።
ከአባይ ወንዝ ተገቢውን ጥቅም እንዳይገኝ ካደረጉ ነገሮች መካከል የፕሮጀክት ማስፈጸሚያ ገንዘብ እጦት፣ የእርስ በርስ ጦርነትና የዓለም ፖለቲካ ተለዋዋጭ አሰላለፍ የሚጠቀሱ ናቸው።
በኢትዮጵያ ላይ ሁለንተናዊ ጫና ለመፍጠር በሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽነት እንዲሁም በሰላምና ሰብዓዊ መብት ስም ተጽእኖ ሲደረግ ይስተዋላል።
ከለውጡ በኃላም የሚሰሩ ስራዎችን ወደ ኋላ የሚጎትቱት በዲፕሎማሲ ስም የሚመጡ ጫና ነው።
በአሸባሪነት የተፈረጀው ጁንታ የጥፋት እንቅስቃሴን የዲፕሎማሲ አጋሮቻችን በቀላሉ ተመልክተው ጫና ሲያደርጉ ይታያል።
በዚህ ወቅት ኢትዮጵያኖች የውስጥ ችግሮች በሊሂቃን ውይይትና ድርድር የሚፈቱበትና እነዚህም የጊዜ ጉዳይ እንጂ እንደሚፈቱ አያጠራጥርም ብሏል በመልእክቱ።
የውጪው ፈተና ግን ጊዜ የሚሰጥ ባለመሆኑና ከግራም ከቀኝም የተቃጡትን አደጋ ለመቀልበስ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ እንደ አንድ ልብ መስካሪ ሆነን የምንቆበት ወቅት ነው ብሏል።
ምርጫው ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም አካላት አስፈላጊውን ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።
አንድ ሆነን እንደ ብዙ ብዙ ሆነን እንድ አንድ በመንቀሳቀስ የጀመርናቸውን ፕሮጀክቶች ሁሉ በተገቢው ደረጃና ፍጥነት ማጠናቀቅ አለብን ብሏል።