ቀጥታ፡

በሀገሪቱ በበጀት ዓመቱ ከ15 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ መንገዶች መጠገናቸው ተገለጸ

አዳማ ግንቦት 20/2013( ኢዜአ) በሀገሪቱ በበጀት ዓመቱ ያለፉት ዘጠኝ ወራት በመደበኛና ወቅታዊ ጥገና ከ15 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ መንገዶች መጠገናቸውን የመንገድ ፈንድ ጽህፈት ቤት ገለጸ።

ጽህፈት ቤቱ ተቋማዊ ለውጥና ሪፎርም ለማድረግ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የህንፃ ኮሌጅ ጋር በመተባበር ያካሄደው ጥናት  ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የትራንስፖርት ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቋሚ ኮሚቴ አመራሮችና አባላት ዛሬ በአዳማ ከተማ አቅርቧል።

በዚህ ወቅት የጽህፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ረሺድ ሙሐመድ በተለይ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በሀገሪቱ ጥገና ከሚያስፈልገው መንገድ መድረስ የተቻለው 50 በመቶውን  ብቻ ነው።

ይህም ሆኖ  ባለፉት ዘጠኝ ወራት  ከ15 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ መንገዶች ሲጠገኑ ለዚህም ስራ  ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ገልጸዋል።

በመደበኛና ወቅታዊ ጥገና ለማከናወን ከተያዘው እቅድ አንፃር 83 በመቶው ፤ የመንገድ ጥገና ሀብት ከማሰባሰብ አኳያ 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ ደግሞ የእቅዳችን 90 በመቶ ማሳካት ችለናል ብለዋል።

ተቋማዊ ለውጥና አደረጃጀት በማከናወን አሁን የሀገሪቱ የመንገድ ልማትና እድገት የደረሰበትን ደረጃ የሚመጥን አቅም ለመፍጠር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህንፃ ኮሌጅ ጋር በመተባበር ጥናት አካሄደናል ሲሉ አስረድተዋል።

ለመንገድ ጥገና የሚጥቀውን ከፍተኛ ወጪና የሚመደበው ፋይናንስ ያለመጣጣም፣ በአቅምና በአፈፃፀም የተሻለ የሚሰራ  አካል ያለመኖር በጥናቱ የተለዩ ቁልፍ ችግሮች መሆናቸውን አመልክተዋል።

የክልሎችን የመንገድ ኤጄንሲዎች የጥገና አቅም ለማጠናከር 38 የተለያዩ ማሽኖች በ600 ሚሊዮን ብር በመግዛት በቅርቡ እንደሚያስረክቡ አስታውቀዋል።

በተጨማሪም ባለፉት ዘጠኝ ወራት የኢትዮጵያ መንገዶች ኔትዎርክ ስርዓት መዘርጋት መቻሉን ጠቅሰው ይህም ስለመንገዶች በያሉበት ሆነው በቀላሉ ማንኛውም አካል መረጃውን የሚያገኝበት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህንፃ ኮሌጅ የተካሄደውን ጥናት የመሩት ዶክትር በቀለ ንጉሴ በበኩላቸው፤ የመንገድ ልማትና እድገቱ የተሻለ ደረጃ ላይ ቢሆንም ሀብቱ በዘላቂነት አገልግሎት እንዲሰጥ የሚያስችል የጥገናና አያያዝ ስራ ባለበት መቆሙንም አስረድተዋል።

ሀገሪቱ እስካሁን ከ17 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሀብት በማፍሰስ ከ24 ዓመታት በፊት የነበረውን 24ሺህ ኪሎሜትር ወደ 144ሺህ ኪሎሜትር ማሳደግ መቻሏን ያወሱት ዶክተር በቀለ፤ ሀብቱ ከጥቅም ውጪ ሳይሆን ተከታታይ፣ በቂና ዘላቂ ጥገና ያስፈልጋል ብለዋል።

ጥናቱ የመንገድ ፈንድ አደረጃጀትና አሰራር ያለበትን ክፍተት፣ የሀብት አሰባሰብ ውስንነት፣ የጥገና ልምድ  ዘመናዊና ፈጣን ያለመሆንን ጠቅሰዋል።

እየተሰበሰበ  ባለው ሀብት ለመንገዶች  የተሟላ ጥገና ቢደረግ 20 በመቶ ብቻ የሚሸፍንና ይህም በእጅጉ አነስተኛ መሆኑን ዶክተር በቀለ ገልጸዋል።

የመንገድ ጥገና አደረጃጀት ከ24 ዓመታት በፊት የተሰራ በመሆኑ አሁን የሀገሪቱን የመንገድ ልማትና እድገት ከደረሰበት ደረጃ ጋር ፈፅሞ የሚሄድ መዋቅር አይደለም ብለዋል።

የመንገድ ልማትና እድገቱ በየዓመቱ 10 በመቶ እያደገ በመሆኑ አሁን ባለው አሰራርና አደረጃጀት የመንገድ ደህንነት ማስጠበቅ እንደማይቻል ጠቅሰው ችግሮቹን ለመፍታት ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች በጥናቱ መለየታቸውንም አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም