የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ ያሳለፈው የውሳኔ ሃሳብ ሽብርተኝነትን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ያላገናዘበ ነው… የህግ ባለሙያዎች - ኢዜአ አማርኛ
የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ ያሳለፈው የውሳኔ ሃሳብ ሽብርተኝነትን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ያላገናዘበ ነው… የህግ ባለሙያዎች
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 20/2013(ኢዜአ) የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ ያሳለፈው የውሳኔ ሃሳብ ሽብርተኝነትን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ያላገናዘበና ሃላፊነት የጎደለው ተግባር መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የህግ ባለሙያዎች ተናገሩ።
የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል የተካሄደውን የህግ ማስከበር ዘመቻ መንስኤዎችና የደረሱ ጉዳቶችን ለዓለምአቀፉ ማህበረሰብ በማስገንዘብ በኩል ያሳየው ክፍተት ለውሳኔው ገፊ ምክንያት መሆኑንም የህግ ባለሙያዎቹ አንስተዋል።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የህግ ባለሙያዎች እንዳሉት የአሜሪካ ሴኔት በኢትዮጵያ ላይ ያሳለፈው የውሳኔ ሀሳብ ሽብርተኝነትን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ያላገናዘበና ሃላፊነት የጎደለው ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣናው ሽብርተኝነትን በመከላከልና በሰላም ማስከበር ተልእኮዋ አርአያነት ያለው ተግባር እየፈፀመች መሆኑን የጠቀሱት ባለሙያዎቹ፤ በሽብርተኝነት የተፈረጀውን የህወሓት ቡድን ተዋጋች በሚል ለማእቀብ መነሳታቸው ተገቢነት የለውም ብለዋል።
የህግ ባለሙያው አቶ ሞላልኝ መለሰ "ውሳኔው አሁን ካለው የአገራት የግንኙነት መርህ አኳያ ተቀባይነት የሌለውና የሁለቱን አገሮች የረጅም ጊዜ ወዳጅነት ግምት ውስጥ ያላስገባ፤ የኢትዮጵያንም ሚና የካደ ነው" ብለዋል።
የአሜሪካ ሴኔት የውሳኔ ሃሳብ ሽብርተኝነትን ለመከመላከልና ለመቆጣጠር በዓለም አቀፍ ደረጃ የተዘረጋውን ስርዓት የሚጎዳ ስለመሆኑም አንስተዋል።
አሜሪካና ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሽብርተኝነትን የመከላከል አባል መሆናቸውን ያስታወሱት አቶ ሞላልኝ፣ ውሳኔው አሁን ላይ ከትብብር ይልቅ ወደሽብር ተግባር ለገባው ህወሓት እድል የሚሰጥና ቀጣናውን ስጋት ውስጥ ሊጥል የሚችል ተግባር መሆኑን አብራርተዋል።
የአሜሪካ ሴኔት የመፍትሄ ሀሳብ በሚል የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ አክቲቪስቶችና ጋዜጠኞች ይፈቱ በሚል ያነሳው ሃሳብም የኢትዮጵያን ሉአላዊነት የሚጋፋ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የዓለም አቀፍ ህግ ተመራማሪና መምህር ዶክተር ግርማ ግዛው በበኩላቸው የባለስልጣናት ቪዛ መከልከልና ዲፕሎማቶችን ማስወጣት በየትኛውም አገር የተለመደ ተግባር ነው ይላሉ።
ይሁንና አሜሪካ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ባለስልጣናት ላይ የቪዛ እገዳ ማድረጓ ‘’ሽብርተኛው የህወሓት ቡድን ለምን ተነካ‘’ የሚልና የኢትዮጵያን ሚና የካደ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የተጀመረው ሁሉን አቀፍ ለውጥ በበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት መደነቁን አስታውሰው፤ በተቃራኒው የኢትዮጵያን ብሎም የአፍሪካን ልማትና ዕድገት የማይፈልጉ መኖራቸውን አብራርተዋል።
ከህግ ማስከበር ዘመቻው በፊት በትግራይ ክልል አስተዳደር የመንግስትን ሃይል የሚገዳደር የጦር መሳሪያ ትንኮሳዎችን ሲያደርግ እንደነበር ያስታወሱት ባለሙያዎቹ፣ ይህ አልበቃ ብሎ በአገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን እዝ ላይ አሰቃቂ ጥቃት መፈፀሙን ተናግረዋል።
ተግባሩ በየትኛውም አገር ተቀባይነት የሌለውና ከባድ ወንጀል መሆኑን ጠቅሰው፣ መንግስት እንዲህ አይነት ጉዳይ ሲያጋጥመው ህግ የማስከበር ስራን ብቸኛ አማራጭ አድርጎ መውሰዱ ግዴታው ነው ብለዋል።
ይሁንና ከመነሻው እስከ መድረሻው ያለውን የህግ ማስከበር ሂደት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብና መንግስታት በአግባቡ ማስገንዘብ ላይ በቂ ሥራ አልተሰራም የሚል እምነት እንዳላቸው ገልፀጸዋል።
መንግስት አሸባሪ ድርጅት ብሎ የፈረጀውን ድርጅት ከራሱ ጋር እንደገና ተባብረህ ተጋግዘህ ስራ ብሎ ጥሪ ማድረግም መሰረታዊ ስሀተት ነው ያሉት የህግ ባለሙያው አቶ ሞላልኝ መሰለ፤ የአሜሪካ የሴኔት ምክር ቤቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው እውነታ በትክክል ሳይገነዘብ ውሳኔ ላይ መድረሱን ያሳያል ብለዋል።
ኢትዮጵያና አሜሪካ የረጅም ጊዜ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው አገራት እንደመሆናቸው ግንኙነታቸውን ከሚያሻክር ይልቅ የሚያቀራርብ ሥራ መስራት እንደሚገባም የህግ ባሙያዎቹ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት አለምአቀፍ ህብረተሰብ የሴኔት ምክር ቤቱ ውሳኔ ምን ያህል ስህተት እንደሆነና እውነታውን እንዲረዳ በማድረግ የነበረውን የዲፕሎማሲ ክፍተቶች በደንብ በመፈተሽ ክፍተቱ ሊሞላ በሚችል መልክ ሰፊ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸውም ነው አቶ ሞላልኝ ያመለከቱት።
የአሜሪካ ሴኔት በትግራይ ክልል የተካሄደውን የህግ ማስከበር ዘመቻ ተከትሎ የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ላይ የቪዛ እቀባ በማድረጉ ኢትዮጵያዊያን በያሉበት እያወገዙት ይገኛሉ።