የአስአሌ አወዳይ ጨው ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ስራ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የአስአሌ አወዳይ ጨው ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ስራ ጀመረ
ሰመራ፤20 /2013(ኢዜአ) በአፋር ክልል በ400 ሚሊዮን ብር የተገነባው የአስአሌ አወዳይ ጨው ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ተመርቆ ስራ ጀመረ።
በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ አወል አርባ የተመረቀው ይሄው ፋብሪካ በአካባቢው ለሚገኙ ከ270 በላይ ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል መፍጠሩን የፋብሪካው ስራ አስኪያጅ አቶ ተሰማ ጌታቸው ትናንት በተካሄደው የምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ ገልጸዋል።
የፋብሪካው ግንባታ ከሁለት ዓመት በላይ እንደወሰደ ያመለከቱት ስራ አስኪያጁ፤ በግማሽ እና አንድ ኪሎ ግራም የተዘጋጀ ሰባት ዓይነት በአዮዲን የበለፀገ የጨው ምርቶችን ለገበያ እንደሚያቀርብ ተናግረዋል።
ፋብሪካው በ30ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ መሆኑን ጠቁመው በወር ከ400ሺህ ኩንታል በላይ በአዮዲን የበለጸገ ጨው በማምራት ለተጠቃሚው የማቅረብ አቅም አለው ብለዋል ።
ስራውን የሚያካሄዱት በአከባቢው ከሚገኙ ባህላዊ የጨው አምራቾች ጥሬ የጨው ምርት በመግዛት የገበያ ትስስር በመፍጠር እንደሆነ ስራ አስኪያጁ ገልጸዋል።
ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር የአካባቢው አርብቶ አደር ልጆች በማህበር ተደራጅተው ምርቱን በራሳቸው ለሸማቹ በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከክልሉ መንግስት ጋር እንደሚሰሩም ጠቁመዋል።
የፋብሪካው ግንባታ እውን መሆን የክልሉና ፌደራል መንግስት እንዲሁም የአካባቢው ህብረተሰብ ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑንም አስታውቀዋል።