የምርት ጥራትና ተጨማሪ እሴት ጉድለት የአገሪቱን የወጪ ንግድ መጉዳቱ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የምርት ጥራትና ተጨማሪ እሴት ጉድለት የአገሪቱን የወጪ ንግድ መጉዳቱ ተገለጸ
አዲስ አበባ ሀምሌ 27/2010 በኢትዮጵያ ጥራት ያላቸው እና እሴት የታከለባቸው ምርቶችን ማቅረብ አለመቻሉ የወጪ ንግድ እንዲዳከም አንዱ ምክንያት መሆኑን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለፀ። ሚኒስቴሩ "ጥራት ያለው ምርትና አገልግሎት እንዲኖር ተቀናጅተን እንስራ" በሚል መሪ ቃል ከኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት ጋር በመተባበር ያዘጋጀውና የሚመለከታቸው ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች የተሳተፉበት ውይይት አካሂዷል። በውይይቱ ላይ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያ እንደተናገሩት፤ በአንድ አገር ጤናማ ምጣኔ ኃብታዊ እንቅስቃሴ እንዲኖር በአገር ውስጥ ከሚመረተው ጠቅላላው ምርት ቢያንስ 30 በመቶ ያህሉን ለውጭ ገበያ የማቅረብ አቅም ሊኖር ግድ ይላል። ያም ሆኖ ግን ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ለውጭ ገበያ የምታቀርበው የምርት መጠን ከ10 በመቶ ያነሰ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩ "ለዚህም ምክንያቱ ጥራትና እሴት የተጨመረባቸው ምርቶችን ለዓለም ገበያ ማቅረብ አለመቻላችን ነው" ብለዋል። በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ የወጪ እና የገቢ ንግድ ሚዛን ልዩነት በእጅጉ ሰፊ መሆኑንም ሚኒስትሩ አንስተዋል። ''ይህ ደግሞ ምጣኔ ኃብታዊ ሁኔታው አደጋ ላይ መሆኑን ያሳያል'' የሚሉት ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን የጥራት ሰርተፍኬት ሳይኖራቸው ጥራትና እሴት ያልተጨመረበት ምርት ይዘው ወደ ዓለም ገበያ የሚቀርቡ አካላት ለችግሩ መከሰት ምክንያት መሆናቸውን አስረድተዋል። ኢትዮጵያ ጥራትና እሴት የተጨመረባቸው ምርቶችን ለዓለም ገበያ ማቅረብ ካልቻለች ምጣኔ ኃብታዊ እድገትን ማረጋገጥ ፈታኝ እንደሚሆንም አስገንዝበዋል። "የአገሪቱ ምርቶች የዓለም ገበያን ጥራት ደረጃ ባለማሟላታቸው ገዢ አጥተው ይመለሳሉ፤ በዚህም አገሪቱ ለኪሳራ እየተዳረገች ነው" ያሉት ሚኒስትሩ ላኪዎች ጥራቱ ያልተረጋገጠና የጥራት ምስክር ወረቀት ያላገኙ ምርቶቻቸውን ወደ ውጪ እንዳይልኩ አሳስበዋል። የንግድ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር መብራህቱ መለሰ በበኩላቸው በንግድ ለተሰማሩ ኩባንያዎች ፈቃድ የሚሰጠው ከሚመለከታቸው አካላት ዘንድ የብቃት ማረጋገጫ ይዘው ለሚቀርቡ ብቻ ቢሆንም በህገ-ወጥ መንገድ ለውጪም ሆነ ለአገር ውስጥ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል። ጥራትን ጨምሮ የተለያዩ ከግብይት ጋር የተያያዙ ችግሮችን መከላከል ብሎም መቆጣጠር የሚቻለው የሁሉም ህብረተሰብ ተሳትፎ ሲታከልበት መሆኑን ገልፀዋል። የጥራት ደረጃና ምደባ የሚሰጡ ተቋማትም በንግድ መስተጋብሩ ውስጥ የሚታዩትን ችግሮች ለመከላከል የሚያስችሉ ማህበረሰባዊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራትን በስፋት ማከናወን እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል። የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተሻለ በልሁ እንዳሉት ህብረተሰቡ የሚሸምታቸው ምርቶች የጥራት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ያላቸው ስለመሆናቸው እንዲያረጋግጥ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ይሰራል።