የሞጆ ደረቅ ወደብና ተርሚናል የሎጀስቲክ ሃብ እንዲሆን እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሞጆ ደረቅ ወደብና ተርሚናል የሎጀስቲክ ሃብ እንዲሆን እየተሰራ ነው
ግንቦት 20/2013 (ኢዜአ) የሞጆ ደረቅ ወደብና ተርሚናል የሎጀስቲክ ሃብ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጀት ገለጸ።
የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ከሚያስተዳድራቸው 8 ወዶቦች አንዱ የሞጆ ደረቅ ወደብና ተርሚናል ነው።
የትራንስፖርት ሚኒስቴር በሥሩ ያሉ ተጠሪ ተቋማት እያከናወኑ ያሉትን የመንገድ፣ የባቡር፣ የደረቅ ወደብ አገልግሎት እና የመሠረተ ልማት ሥራዎች ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እያስጎበኘ ይገኛል።
የሞጆ ደረቅ ወደብና ተርሚናል የአገሪቱን በርካታ የገቢ ዕቃዎች የሚያስተናገድ ቢሆንም አሁን ላይ የወጭ እቃዎችንም አገልግሎት የሚሰጥበት (የሎጀስቲክ ሃብ) ለማድረግ እየተሰራ ነው።
የሞጆ ደረቅ ወደብና ተርሚናል ኃላፊ አቶ ደረጀ ሚደቅሳ እንደገለጹት አገልግሎቱ የገቢ እቃዎችን በመቀበል ብቻ ሳይገደብ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን አሽጎ በመላክ የውጭ ንግድን ለማሳለጥ እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የወደብ ቆይታን በማሳጠር የጊዜ፣ የጉልበት እንዲሁም የደህንነት ጉዳዮችን ያሟላና በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት ለመሥጠት እንደሚያግዝም አብራርተዋል ።
በዚህም ወደ ወጭ የሚላኩ የወጪ ምርቶች በተለይ ቡና ላይ የሚደረግ ቅሸባና ስርቆትን ማዳን ይቻላል ብለዋል።
ወደቡ ይህን አገልግሎት መስጠት እንዲያስችለው በ150 ሚሊዮን ዶላር የማስፋፊያ ስራ እየተከናወነለት መሆኑ ታውቋል።
የሞጆ ደረቅ ወደብና ተርሚናል የአገሪቱን 80 በመቶ የገቢ እቃዎች እያስተናገደ መሆኑ ይታወቃል።