የህክምና ዘርፉን አማራጭ የቱሪዝም ሃብት ማድረግ እንደሚገባ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስገነዘበ - ኢዜአ አማርኛ
የህክምና ዘርፉን አማራጭ የቱሪዝም ሃብት ማድረግ እንደሚገባ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስገነዘበ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19 ቀን 2013 (ኢዜአ) በህክምናው መስክ ያለውን አቅም በማስፋት አማራጭ የቱሪዝም ሃብት ማግኛ ማድረግ እንደሚገባ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው ገለጹ።
በዋጋ ሜዲካል ሰርቪስ እና በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ትብብር በተዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ ዶክተር ሂሩት እንደገለጹት፤ የህክምና ዘርፉን አማራጭ የቱሪዝም ሃብት ማድረግ ያስፈልጋል።
"የግል ባለሀብቶች ዘርፉን በማዘመንና በማስፋፋት ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል" ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች የቱሪዝም ፍሰቷን እያሳደገች ብትመጣም በህክምና ቱሪዝም ዘርፍ እያከናወነች ያለው ተግባር ዝቅተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ "በተለይ በባህል ህክምናው ዘርፍ ያልተነካውን ሀብት መጠቀም ይገባል" ብለዋል።
ኢትዮጵያ ዘመናዊ፣ ባህላዊ እና መንፈሳዊ ህክምናዎቿን ለዓለም ማህበረሰብ በማስተዋወቅ በዘርፉ የምታገኘውን ገቢና የውጭ ምንዛሪ ለማሳደግ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
የዋጋ የሕክምና አገልግሎት ማዕከል መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር መልዓኩ ጋሜ በበኩላቸው፤ "ኢትዮጵያ በህክምና ቱሪዝም ዘርፍ ያላትን እምቅ ሀብት መጠቀም ከቻለች ለውጭ ምንዛሪ ግኝትና ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር ያስችላል" ብለዋል።
የተሟላ የህክምና መሳሪያዎችን በማስመጣትና ብቃት ያለው የሰው ኃይል በማዘጋጀት ጥሩ ተወዳዳሪ በመሆን ዘርፉን ማዘመንና ማሳደግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ዋጋ የህክምና አገልግሎት ለተለያዩ ጎረቤት ሀገራት የህክምና አገልገሎት በመስጠት የውጭ ምንዛሪ እያስገኘ መሆኑ ተገልጿል።