የኢትዮጵያ ጦር አልሸባብን በመደምሰስና የሽብር ኢላማውን በማክሸፍ ቀጣናውን እያፀዳ መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ጦር አልሸባብን በመደምሰስና የሽብር ኢላማውን በማክሸፍ ቀጣናውን እያፀዳ መሆኑ ተገለጸ
ግንቦት 19 ቀን 2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ጦር አልሸባብን በመደምሰስና የሽብር ኢላማውን በማክሸፍ ቀጣናውን እያፀዳ መሆኑን የአሚሶም ኃይል አዛዥ ሌ/ጄ ዳዮመንዴ ንደገያ ገለፁ።
አዛዡ በሶማሊያ ስላለው ወቅታዊ የሠላም ማስከበር ሁኔታና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ከኢፌዴሪ መከላከያ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ጋር ተወያይተዋል።
በምክክሩ ወቅት የመከላከያ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል ብርሃኑ ጁላ በቀጣናው ሠላምን ለማስፈን ቅንጅታዊ አሠራሮችን አጠናክሮ ማስቀጠል እና ዘላቂ ሠላምን ለማስፈን የሶማሊያ ፀጥታ ኃይልን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የአሚሶም ኃይል አዛዥ ሌ/ጄ ዳዮመንዴ ንደገያ የኢትዮጵያ ጦር አልሸባብን በመዋጋት እያሳየ ያለውን ጀግንነት አድንቀው፤ ቀጣናውን ሠላማዊ ለማድረግ ቅንጅታዊ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አመላክተዋል።
በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት የመከላከያ የውጭ ግንኙነት ዳይሬክተር ብ/ጄ ቡልቲ ታደሰ የፀጥታ ኃይሉ እየወሰደ ባለው ዕርምጃ አልሸባብ እየተዳከመ መሆኑ እና በተለያዩ ቀጣናዎች ያቀዳቸው የሽብር ተልዕኮዎች መክሸፋቸውን በውይይቱ መዳሰሱን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ጦር በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ከማስጠበቅ አልፎ ወደ ሶማሊያ ዘምቶ ዓለም አቀፍ አሸባሪ በሆነው አልሸባብ ላይ የኃይል ዕርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ገልጿል።