መንግሥት በማህበራዊ ሚዲያ የተሳሳተ መረጃ በሚያሰራጩ ሰዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ ካልወሰደ ኢትዮጵያን ወደ ቀውስ ይከታታል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
መንግሥት በማህበራዊ ሚዲያ የተሳሳተ መረጃ በሚያሰራጩ ሰዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ ካልወሰደ ኢትዮጵያን ወደ ቀውስ ይከታታል ተባለ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19 /2013 (ኢዜአ) መንግሥት በማህበራዊ ትስስር ገጾች የሚለቀቁ ሐሰተኛ መረጃዎችን በሕግ መቆጣጠር ካልቻለ ኢትዮጵያን ወደ ባሰ ችግር ውስጥ እንደሚከታት ኢዜአ ያነጋገራቸው የመዲናዋ ነዋሪዎች ገለጹ።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን በበኩሉ የበይነ መረብ ሚዲያዎችን ወደ ህጋዊ አሰራር የሚያስገባ ስርዓት ማበጀቱን ጠቁሞ፤ ይህን በማይተገብሩት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ገልጿል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በማህበራዊ ትስስር ገጾች የሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎች የሰውን ትኩረት ከመቼውም ጊዜ በላይ እየሳቡ የሚገኝ ሲሆን ጉዳዩም የዓለም መንግስታት የወቅቱ ፈተና ሆኗል።
በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎቹ የሚለቀቁ ሀሰተኛ መረጃዎችን ሰዎች አስፈላጊውን ማጣራት ሳያደርጉ እንደወረደ ተቀብለው መልሰው ሲያሰራጩ ይታያል።
መረጃዎችን ሳያጣሩና ሳያረጋግጡ ለሌሎች የማጋራት ዝንባሌ ነገሮችን አደገኛ እንደሚያደርጋቸውና በግለሰብ፣ በቤተሰብና በአጠቃላይ እንደ ማህበረሰብ ጉዳት እንደያደርሱ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
የዓለም መንግስታት የሀሰተኛ መረጃዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሕግ ማዕቀፎችን በማውጣት እርምጃ ወደ መውሰድ ገብተዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችም በኢትዮጵያ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚተላለፉ የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱንና በማህበረሰቡ መካከል ግጭቶችና አለመግባባቶች እየፈጠሩ እንደሆነ ገልጸዋል።
ሀሰተኛ መረጃ የሚያሰራጩ ግለሰቦችን ተጠያቂ በማድረግ ረገድም መንግስት ቸልተኝነት እንደሚታይበት ተናግረዋል።
"መንግስት ሀሰተኛ መረጃ በሚያሰራጩ ላይ አስፈላጊውን እርምጃ ባለመወሰዱ የችግሩ መጠን እየሰፋ መጥቷል" ብለዋል አስተያየት ሰጭዎቹ።
በመሆኑም የሀሰተኛ መረጃዎችን በሕግ መቆጣጠር ካልተቻለ ኢትዮጵያን ወደ ባሰ ችግር ውስጥ ሊከታት እንደሚችል ገልጸው፤ መንግስት ይህን ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎችን በሕግ ተጠያቂ ማድረግ እንዳለበት ጠቁመዋል።
መንግስት ሀሰተኛ መረጃን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከሚወስደው ሕጋዊ እርምጃ በተጨማሪ የማህበረሰቡን የማህበራዊ ትስስር ገጾች አጠቃቀም ንቃተ ሕሊና ለማሳደግ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባም አንስተዋል።
ዜጎች ሀሰተኛ መረጃዎች ሲያጋጥሟቸው ማሳወቅ የሚችሉባቸው የአሰራር ስርዓቶች መዘጋጀት እንዳለበትም ጠቁመዋል።
ዜጎች በማህበራዊ ትስስር የሚደርሷቸውን ያልተረጋገጡ መረጃዎች ማጣራት እንዲሁም ሀሰተኛ መረጃዎችን ከማጋራት መቆጠብ እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ ኢድሪስ በበኩላቸው ህግና ስርዓትን ጠብቀው የሚሰሩ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን እንዳሉ ሁሉ ለዜጎች አብሮነትና ለሀገር ህልውና ግድ የማይሰጣቸው መኖራቸውን ገልጸዋል።
መንግስት ዘርፉን በህግ ለመምራት አዋጅ አዘጋጅቶ ወደ ስራ መግባቱንም ነው ያነሱት።
በአዋጁ መሰረትም የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን እንዲመዘገቡ ጥሪ መቅረቡን ገልጸው፤ "እስካሁን ባለው ሂደት 28 የሚሆኑት ተመዝግበው ወደ ህጋዊ አሰራር ገብተዋል" ብለዋል።
ተመዝግበው ወደ ህጋዊ ስርዓት ለገቡት ስልጠናን ጨምሮ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ጠቁመዋል።
"በህገ ወጥ መንገድ ህዝብን ከህዝብ በማጋጨት በሀገር ህልውና ላይ አደጋ በመጣል በሚንቀሳቀሱት ላይ ከሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት ጋር በመቀናጀት ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳል" በማለት ባለስልጣኑ ያለውን ዝግጁነት ገልጸዋል።
ዜጎች ጥላቻና የሃሰት መረጃ የሚያሰረጩ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃንን ባለመከተልና መልእክቶቻቸውን ባለማጋራት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።