ቀጥታ፡

ከፓርቲ ጥቅምና ፍላጎት የአገር ደህንነት ይቀድማል- ኢዜማ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19 ቀን 2013 (ኢዜአ) ከፓርቲ ጥቅምና ፍላጎት የኢትዮጵያ ደህንነት ይቀድማል ሲል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ ገለጸ።

ፓርቲው አጠቃላይ የምርጫ ሂደቱን አስመልክቶ 'ከፓርቲ ጥቅምና ፍላጎት የአገር ደህንነት ይቀድማል' በሚል ርዕስ መግለጫ ሰጥቷል።

ፓርቲውን ወክለው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩት አቶ ዘላለም ወርቃገኘሁ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በትውልድ ቅብብሎሽ የሚገነባ ነው ይላሉ።

ፓርቲውም ዘንድሮ የሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ያግዛል ብሎ ያምናል ብለዋል።

በዚህ ወቅት በአገሪቱ የተደራረቡ ችግሮች የሚፈቱት በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት ሲመሰረት መሆኑን ገልጸዋል።

በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት ለመመስረት ደግሞ አንዱ አማራጭ ዴሞክራሲያዊ ምርጫን ማከናወን መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ በሕዝብ የተመረጠ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ለመመስረት በሚደረገው ሂደት ሰላማዊ ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ፓርቲው አረጋግጧል።

ፓርቲው እስካሁን ባደረገው የምርጫ እንቅስቃሴ አጠቃላይ ሂደቱ ላይ የተለያዩ ችግሮች እያጋጠሙት መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ ሂደት ''በምርጫው ያለንን አገርን የማሻገር እምነት በመሸርሸር አገሪቱ ካለችበት ውስጣዊና ውጫዊ ጫናዎች እንዲሁም ፈታኝ ሁኔታዎች ለመወጣት ያለውን ተስፋ ያደበዝዛል'' ሲሉም አክለዋል።

በመሆኑም ገዢው ፓርቲ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀው፤ እያንዳንዱ ዜጋም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱን ለማቆም ይበጀኛል ያለውን መምረጥ እንዳለበት አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም