አራት አመት ለዘገየው የሚዛን አማን አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ሌላ ተለዋጭ ቦታ መጠየቁ ቅሬታ ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
አራት አመት ለዘገየው የሚዛን አማን አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ሌላ ተለዋጭ ቦታ መጠየቁ ቅሬታ ፈጥሯል
ሚዛን፣ ግንቦት 19/2013 (ኢዜአ) የሚዛን አማን አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ሳይጀመር ለአራት አመት በመቆየቱ ቅሬታ የፈጠረባቸው መሆኑን የከተማው ነዋሪዎች ገለፁ ።
ለአውሮፕላን ማረፊያው ግንባታ ከይዞታቸው ለተነሱ ነዋሪዎች 29 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር የካሳ ክፍያ መፈጸሙን የገለጸው የቤንች ሸኮ ዞን አስተዳደርም በግንባታው አለመጀመር የፈጠረውን ቅሬታ አስታውቋል።
የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪ አቶ ግርማ ባሻ ለኢዜአ እንዳሉት የአውሮፕላን ማረፊያውን ግንባታ ቦታ እንዲለቁ ከተደረገ አራት አመት ተቆጥሯል።
"የግንባታውን መጀመር በጉጉት ስንጠብቅ ብንቆይም አሁን ላይ የሰማነው ለግንባታው የሚሆን ሌላ ተቀያሪ ቦታ ይፈለግ የሚል ወሬ ይዞታችንን በመልቀቅ የከፈልነውን ዋጋ አሳጥቶናል" ብለዋል።
"በወቅቱ ይሆናል ተብሎ ታምኖበት ስፍራው ለግንባታው ነጻ ከተደረገ በኋላ ወደ ስራ መግባት የሚቻልበትን ጊዜ አሳልፎ ሌላ ጥያቄ ማቅረብ ተገቢ አይደለም ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
ዞኑ ከአዲስ አበባ ያለውን ርቀት ግምት ውስጥ በማስገባት የአይውፕላን ማረፊያው ግንባታ በፍጥነት እንዲጀመር ጠይቀዋል።
ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ትዕግስት አሰፋ በበኩላቸው "አውሮፕላን ማረፊያው ይገነባል ከተባለ አራት ዓመት ካስቆጠረ በኋላ ሌላ ምክንያት መቅረቡ አሳማኝ አለመሆኑን ተናግረዋል።
"ህብረተሰቡ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታውን አስፈላጊነት በማመን ይዞታውን ከመልቀቅ ጀምሮ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተ መሆኑን በመረዳት ግንባታውን በፍጥነት መጀመር ይገባል" ሲሉ አመልክተዋል ።
የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፍቅሬ አማን በወቅቱ ለአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ እንዲሆን ለተመረጠው ቦታ ለልማት ቅድሚያ የመስጠት ዓላማን በመሰነቅ ከቦታው ሰው ብቻ ሳይሆን መካነ መቃብር ጭምር እንዲነሳ መደረጉን ተናግረዋል።
ለግንባታው የተመረጠውን አራት ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን ቦታ ክፍት ለማድረግ ከቦታው ለተነሱ አርሶ አደሮች የዞኑ አስተዳደር 21 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ካሳ መክፈሉን አመልክተዋል።
በተጨማሪም አስተዳደሩ ከይዞታቸው ለተነሱ ነዋሪዎች ለመኖሪያና ለእርሻ የሚሆን 120 ሄክታር መሬት መስጠቱን ጠቅሰዋል፡፡
የዞኑ አስተዳደር የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታው እንዲጀመር ለኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት በተደጋጋሚ ለሚያቀርበው ጥያቄ ግንባታውን ለማስጀመር በጨረታ ሂደት ላይ ነን የሚል ምላሽ ሲሰጠው መቆየቱን አውስተዋል ።
ድርጅቱ አሁን ላይ ያቀረበው የሌላ ቦታ ቅያሪ ጉዳይ ተገቢነት እንደሌለው ጠቁመው አስተዳደሩ በጉዳዩ ማዘኑን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ እስክንድር አለሙ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ "ጨረታ አውጥተን ስራውን ለመጀመር እየተዘጋጀን ባለንበት ወቅት ቦታው ለግንባታ ምቹ ሳይሆን ቀርቷል" ብለዋል ።
ቦታው ምቹ ባለመሆኑ የተነሳም ከሌሎች አውሮፕላን ማረፊያዎች በተለየ ከፍተኛ ወጪ የሚያስወጣ ሆኖ መገኘቱን ተናግረዋል።
ድርጅቱ ለግንባታው የሚሆን ሌላ ቦታ እንዲመቻች ጥያቄ ማቅረቡን አመልክተዋል።
የክልሉ መንግስት ሌላ አማራጭ ቦታ መቀየር እንደማይችል በደብዳቤ ማሳወቁን የጠቀሱት አቶ እስክንድር ከክልሉ ጋር በመነጋገር መፍትሄ እንደሚፈለግ አስታውቀዋል።