በመቀሌ ህገወጥ የጎዳና ላይ የቤንዚን ንግድ ለእሳት አደጋ መንስኤ እየሆነ ነው- ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በመቀሌ ህገወጥ የጎዳና ላይ የቤንዚን ንግድ ለእሳት አደጋ መንስኤ እየሆነ ነው- ነዋሪዎች
መቀሌ፣ ግንቦት 19/2013 (ኢዜአ) በመቀሌ ከተማ በህገወጥ መንገድ በጎዳና ላይ እየተካሄደ ያለ የቤንዚን ንግድ ለእሳት አደጋ መንስኤ እየሆነ መምጣቱን ነዋሪዎች ገለጹ።
የከተማው የመንግስት አገልግሎት የንግድ ፅህፈት ቤት በበኩሉ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ችግሩን ለመፍታት እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።
ከከተማው ነዋሪዎች መካከል አቶ ወሰንሰገድ ገብረመድህን ለኢዜአ እንደገለጹት በከተማው በዋና ዋና ጎዳናዎች በመንገድ ዳር በጀሪካንና በፋብሪካ ውሀ ማሸጊያ ፕላስቲክ ጠርሙስ ለሽያጭ እየቀረበ ያለ ቤንዚን በጥንቃቄ ጉድለት ለእሳት አደጋ መንስኤ እየሆነ ነው።
ለሽያጭ እየቀረበ ባለ ቤንዚን በጥንቃቄ ጉድለት የሚከሰት የእሳት ቃጠሎ ለንብረት ውድመት ምክንያት እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል።
በከተማው በጎዳና ዳርቻ ለሽያጭ በቀረበ ቤንዚን በተፈጠረ ቃጠሎ አንድ የኤሌክትሪክ ሀይል ማስተላለፊያ ትራንስፎርመርና ሶስት ባለ ሶስት እግር ባጃጅ ተሽከርካሪዎች መቃጠላቸውን የገለጹት ደግሞ በከተማው የታክሲ ማህበር አባል አቶ ተስፋይ ግርማይ ናቸው።
አቶ ሀጎስ ሀዲሽ በበኩላቸው “በነዳጅ ማደያ በህጋዊ መንገድ በ29 ብር ሲሸጥ የነበረ አንድ ሊትር ቤንዝን በህገወጥ ንግዱ ሀምሳ ብር እየተሸጠ ነው” ብለዋል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የትግራይ ከልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ገብረመድህን ህገወጥ የጎዳና ላይ የቤንዚን ሽያጭ ተከተሎ በተከሰተ የእሳት አደጋ የሀይል ማስተላለፊያ ትራንስፎርመር በመቃጠሉ በአካባቢው የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲቋረጥ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።
በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የመቀሌ ከተማ የመንግስት አገልግሎት የንግድ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ገብረ ኪሮስ ህሉፍ ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው በከተማው የቤንዚን እጥረት መኖሩን ተናግረዋል ።
በዘርፉ የሚታየውን ህገወጥ ንግድ ለማስቀረት ከንግድ ማህበራትና ከፀጥታ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
በከተማው የሚገኙ 11 የነዳጅ ማደያዎች ህግና ስርአትን ጠብቀው ምርቱን በአግባቡ ለተጠቃሚ እንዲያሰራጩና ምርት በሚደብቁ ላይ እርምጃ ለመውሰድ ከነዳጅ ማደያ ባለቤቶች ጋር ውይይት ተደርጎ ከስምምነት መደረሱን ሀላፊው አስታውቀዋል ።