ቀጥታ፡

ኢዜአ ምርጫውን በተመለከተ ሚዛናዊና ትክክለኛ መረጃ ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገለጸ

አዳማ፣ ግንቦት 19/2013-(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) 6ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በተመለከተ ሚዛናዊና ትክክለኛ መረጃ ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገለጸ።

አስተማማኝ የመረጃ ምንጭ ለመሆን እየሰራ ያለው ኢዜአ በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ሚዛኑን የጠበቀ ትክክለኛ መረጃ ለማድረስ የጋዜጠኞችን አቅም ከመገንባት ጀምሮ የተለያዩ ተግባራት እያከናወነ እንደሚገኝ ተገልጿል።

በመላ ኢትዮጵያ መረጃ በማሰባሰብ የሚሰራው ኢዜአ በክልል ለሚገኙ ማስተባበሪያዎችና ቅርንጫፎች ጋዜጠኞቹ በምርጫና በግጭት ነክ ዘገባዎች እንዲሁም በማህበራዊ ሚዲያና በአዲሱ የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ዙሪያ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል።

የስልጠና መድረኩ መክፈቻ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የኢዜአ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ ቤተልሄም አበባው “ተቋሙ በ6ኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ ትክክለኛና ሚዛናዊ መረጃ ለህዝቡ ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ ነው” ብለዋል።

ምርጫውን በተመለከተ የሚሰሩ ዘገባዎችን ትክክለኛነትና ሚዛናዊነት ለማስጠበቅ ጥረት እንደሚደረግም ጠቁመዋል።

የኢዜአ የህዝብ ግኑኝነትና ስትራቴጂክ አጋርነት ዳይሬክተር አቶ ዮሀንስ ወንድይራድ በበኩላቸው “በምርጫ ወቅት ጋዜጠኞች ከማንም አካል ተጽዕኖ ነፃ ሆነው በገለልተኛነት መዘገብ ይኖርባቸዋል” ብለዋል።

በምርጫ ወቅት የጋዜጠኝነት ስነ ምግባርን በጠበቀ አግባብ ገለልተኛ ሆኖ መዘገብ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በተጨማሪም ጋዜጠኞች በማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ላይ ገለልተኛ ሆነው ሙያው የሚጠይቀውን ህግና አሰራር ተከትለው እንዲሰሩ ለማስቻል የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን አመልክተዋል።

በአዲሱ የመገናኛ ብዙኋን አዋጅ ላይ ግልፅ ግንዛቤ አግኝተው ለተሻለ ስራ እንዲዘጋጁ አቅም የማጎልበት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በስልጠናመድረኩ ላይ የኢዜአ የቀጣይ አስር ዓመት ፍኖተ ካርታ መነሻ ፁሑፍ ያቀረቡት ወይዘሮ ብርቅነሽ ዘርፉ በበኩላቸው ተቋሙ የሰው ሃይሉን የማስፈፀምና የመፈፀም አቅም ለማጠናከር፣ ጥራትና ፈጣን መረጃን ለህዝቡ ተደራሽ ለማድረግና ብሔራዊ መግባባትና የሀገር ገፅታን ለመገንባት የሚያስችል እቅድ ማዘጋጀቱን ተናግረዋል።

ኢዜአ በትክክለኛና ሚዛናዊ መረጃ እንዲሁም በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ተደራሽነት በ2022 ዓ.ም ከአፍሪካ ቀዳሚ የመገናኛ አውታር ለመሆን ግብ አስቀምጦ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

እቅዱ ተቋሙ አሁን ካለበት ማነቆ የሚወጣበት በሁሉም መስክ ብቁና ተወዳዳሪ የሚያደርገው እንደሆነም ወይዘሮ ብርቅነሽ ጠቁመዋል።



የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም