በኢትዮጵያና በኤርትራ ላይ የተጣለው ማእቀብ በቀጣናው የአሜሪካን የበላይነት ለማስጠበቅ ያለመ ነው… የፖለቲካ ተንታኞች - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያና በኤርትራ ላይ የተጣለው ማእቀብ በቀጣናው የአሜሪካን የበላይነት ለማስጠበቅ ያለመ ነው… የፖለቲካ ተንታኞች
ግንቦት 13/2013(ኢዜአ) አሜሪካ በኢትዮጵያና በኤርትራ ላይ የጣለችው ማእቀብ ሀገሪቱ በቀጠናው ላይ ያላትን የበላይነት አስጠብቃ ለመቆየት ያላትን ፍላጎት ያሳየ መሆኑን ከብላክ አጀንዳ ሪፖርት ድረገጽ ጋር ቆይታ ያደረጉ የፖለቲካ ተንታኞች ገልጸዋል።
“የውሳኔ ሃሳብ 97 “ በሚል በአሜሪካ ሴኔት ከጸደቀው ውሳኔ መረዳት እንደሚቻለው የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግስት ባለስልጣናት የጉዞ እገዳን ጨምሮ የወታደራዊና ምጣኔ ሃብታዊ እርዳታዎች ላይ ማእቀብ የጣለ ሲሆን የኤርትራ መንግስትም ወታደሮቹን ከትግራይ ክልል በአስቸኳይ ይውጣ የሚል ትዕዛዝ ያስተላለፈ ነው።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይና የሲአይ ኤ መስሪያቤቶች ከፍተኛ ባለስልጣንና የአትላንቲክ ካውንስል ሃላፊ ካሜሮን ሃድሰን ከጥቂት ቀናት በፊት ለፎሬይን ፖሊሲ ሲናገሩ “የምስራቅ አፍሪካዎቹ ኢትዮጵያና ኤርትራ የአሜሪካ ጥቅሞችና ፍላጎቶች በተጻራሪ መቆማቸው የማእቀቡን አስፈላጊነት ያሳያል” ሲሉ ፍንጭ መስጠታቸውን ያስታወሰው ድረገጹ፤ ኢትዮጵ ውሳኔው ሉአላዊነቷን የሚዳፈርና በውስጥ ጉዳዮቿ ጣልቃ የሚገባ በመሆኑ እንዳልተቀበለችው ገልጿል።
ድረገጹ ጄፍ ፒርስ እና ሲሞን ተስፋማርያም ከተባሉ ተንታኞች ጋር ባደረገው ቆይታ ኢትዮጵያ ላይ ጫናው እንዲበረታ የሚፈልጉ ሃይሎች በተናበበ ሁኔታ በርካታ የሐሰት ዘገባዎችን በቴሌግራፍ፣ በሲ ኤን ኤን እና በሌሎች የሚዲያ አውታሮች ሲያሰራጩ መቆየታቸውን መግለጻቸውን አስታውሰዋል።
የአሜሪካ ባለስልጣናት በደሀ ሃገራት ላይ ሊያደርጓቸው የሚፈልጓቸው ተግባራትን ለመፈጸም እንዲያስችላቸው ሰብአዊ መብት፣ ሰላም፣ ዴሞክራሲ እና ፍትህ የመሳሰሉትን አስቀድመው እንደሚያነሱ ያስረዱት ጋዜጠኛና የታሪክ ጸሃፊው ጄፍ ፒርስ፤ የአሜሪካ ባለስልጣናት ራሳቸውን ለማሞኘት የፈጠሩትን ተረት ሌላው እንዲያምናቸው ከመፈለጋቸው የተነሳ አንዳቸው ለሌኛው ምስክር ዳኛና ጠበቃ ሆነው መቅረባቸውን ሚዛናዊ ያልሆኑ የሚዲያ ሽፋኖቻቸውን ማሳያ አድርገው አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለው ሁለንተናዊ ዘመቻ አዲስ አለመሆኑንና በሲአይ ኤ አቀናባሪነት መፈንቅለ መንግስቶች የውክልና ጦርነቶች እንዲሁም በአለም አቀፍ ወንጀል ሰበብ የሚደረጉ እስሮችና ግልጽ ወረራዎች ማሳያዎች መሆናቸውን ያስረዱት ጄፍ ፒርስ፤ ሰብአዊ መብት በሚል ሽፋን አሜሪካና ኔቶ ዩጎዝላቭያ፣ ሊብያና ሶሪያ ላይ የተደረጉት ጦርነቶች ሰብአዊ መብቶችን ከማስከበር ይልቅ አለምን ወደ ባሰ ሰብአዊ ቀውሶች ዳርገዋታል ብለዋል።
በኒውዮርክ የሚኖሩት ኤርትራዊው የህክምና ዶክተርና የዩኒቨርሲቲ መምህር ሲሞን ተስፋማርያም ስለ ጉዳዩ በሰጡት አስተያየት፤ ላለፉት 30 አመታት ህወሃት በአፍሪካ ህብረት የአሜሪካ ጥቅሞች ጉዳይ አስፈጻሚ፣ በአፍሪካ ቀንድ ደግሞ የአሜሪካ ፖሊስ በመሆን ሲላላክ መቆየቱን አስታውሰዋል።
ከሶስት አመታት በፊት በኢትዮጵያ የተደረገው ለውጥ ይሄንን ተግባር ከስሩ የቀየረና የሃገር ሉአላዊነትን ወደ ማስከበር የተመለሰ በመሆኑ የአሜሪካ መንግስት ባለስልጣናትን አላስደሰተም ነው ያሉት።
ህወሃት ለአሜሪካ አስተዳደር የተመቸ ደካማ፣ የተከፋፈለና ብዙሃኑን ያገለለ የአስተዳዳር ስርአት በመመስረት ለ27 አመታት ኢትዮጵያንም ሆነ ምስራቅ አፍሪካን ዋጋ ሲያስከፍል ከመቆየቱም በላይ ኢትዮጵያን ከኤርትራና ከሶማሊያ ጋር ደም አፋሳሽ ጦርነት ውስጥ መክተቱንንም ገልጸዋል።
በዚህም ኤርትራ ላይ ማእቀብ እንዲጣል ማድረጉን ያስታወሱት ዶክተሩ፤ ህወሃት ያሰማራው ኦሮሞዎች የሚበዙበት የጦር ሃይል ፈንጂ ማምከኛ ሆኖ የ80 ሺህ ሰዎች ህይወት እንዳለፈ የሚያሳዩ ማስረጃዎች መኖራቸውን ነው የሚያነሱት።
ህወሃት በኢትዮጵያውያን፣በኤርትራውያንና በሶማሊያውያን ላይ ሲፈጽማቸው የነበሩ ዘግናኝ ወንጀሎችን በመተባበር ያለፈችው አሜሪካ ወደ ምስራቅ አፍሪካ ከምትልከው የጦር መሳሪያ 80 በመቶ የሚሆነው አልሸባብ ጋር እንዲደርስ በማድረግ ሶማሊያ ደካማና ዘላለአለማዊ የአሜሪካ ቅኝ ተገዢ እንድትሆን ያለመ ስለመሆኑም ነው ያብራሩት።
የኤርትራ መንግስት አሜሪካ አካባቢውን ጠቅልላ እንዳትይዝ እንቅፋት ስለሆነባት ማእቀብ በመጣል ሃገሪቱን ለማዳከም ስትሰራ ቆይታለች ሲሉም አስታውሰዋል።
በህወሃት አማካኝነት ፍላጎቷን ያለምንም ጥያቄ ስታስፈጽም የቆየችው አሜሪካ አዲሱ የኢትዮጵያ የለውጥ መንግስት የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎችን አሳሳቦኛል በሚል እንዲያቆም ለማድረግ እየሞከረች ቢሆንም መንግስት በራሱ መንገድ ሉአላዊቱን አስከብሮ በመሄድ ላይ እንደሚገኝ ነው ዶክተር ሲሞን የጠቀሱት።
ዶክተሩ እንደሚሉት “ግብጾች ግድቡን ያፈነዱታል “የሚለውን የትራምፕ አገላለጽ ተከትሎ የመጣው የእርዳታ እገዳ አሜሪካ አሁንም ተላላኪ መንግስት እንደምትፈልግ ጉልህ ማሳያ ነው ብለዋል።
የኤርትራ ጦር ከትግራይ በአፋጣኝ ይውጣ የሚል ትእዛዝ የሰጡት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር አንቶኒዮ ብሊንከን፤ ለእርዳታ ተብሎ ኢትዮጵያ ሉአላዊነቷን አሳልፋ የማትሰጥ ከመሆኑም በላይ ህወሃት የሌለባት ኢትዮጵያና የጎረቤቶቿ ህልውና ላይበጠስ የተሳሰረ እንደሆነ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መስማታቸው ያበሳጫቸው እንዳበሳጫቸውም ገልጸዋል።
የተለመደውን ማእቀብ ኤርትራ ላይ እንዲጣል ማድረጋቸውን የጠቀሱት ዶክተር ሲሞን፤ ሉአላዊቷ ኤርትራ በራሷ መንገድ ለዜጎቼ ይጠቅማል ያለቻቸውን ፖሊሲዎች በማውጣት እያስተገበረች በመሆኑ ከአሜሪካም ሆነ ከቤልጂየም የሚመጡ ትእዛዞችን እንደማትቀበል አንስተዋል።
ሶማሊያን ያካተተው አዲሱ የኢትዮጵያና የኤርትራ ጥምረት ከሚኖረው መልክአምድራዊ ስፋትና ከሚያመጣው አካባቢያዊ ተጽእኖ አኳያ ሁኔታው አሜሪካንን በመገዳደር ለሌሎች የአፍሪካ ሃገራት የሚያስተላልፈው መልእክት ከባድ በመሆኑ የአሜሪካ ባለስልጣናትን ማስከፋቱ ብዙም አይገርምም ነው ያሉት።
ህወሃት በአብዛኞቹ የትግራይ ተወላጆች ባይደገፍም በ1967 ዓ.ም በጻፈው የመመስረቻ ሰነዱ ከኤርትራ ሰፊ መሬት በመውሰድ ትግራይን ከባህር ጋር በማገናኘት ከኢትዮጵያ ተገንጥሎ ታላቋ ትግራይ የምትባል ሃገር በመመስረት ተላላኪነቱን ለመቀጠል አስቦ ሲንቀሳቀስ መቆየቱንም ዶክተሩ አውስተዋል።
በፕሬዝዳንት ባይደን የአሜሪካ አለምአቀፍ የልማት ድርጅት (USAID) የበላይ ሆነው የተሾሙት ሳማንታ ፓወር ቀድመው ባዘጋጇቸው ጋዜጠኞችና የሰብአዊ መብቶች ተማጋች በሚባሉት በኩል የተቀናጁ ዘመቻዎችን ሲያደርጉ መቆየታቸውን ያነሱት ዶክተሩ፤ የለውጥ አራማጆችና ለእውነት የቆሙ የሚዲያ ተቋማት እየተደረገ ስላለው ነገር ዝምታን መምረጣቸው ጥያቄ እንደጫረባቸው ነው የጠቀሱት።
ዶክተሩ ያለንበት ጊዜና ሁኔታ ከአስር አመት በፊት ከነበረው በእጅጉ የተለየና አንዲት ልእለ ሃያል ብቻ የምትፈነጭበት ካለመሆኑም በተጨማሪ ስለኢትዮጵያና ኤርትራ የሚነዙ ውንጀላዎችን ለመመከት የሚያስችሉ የማህበራዊና የመደበኛ ሚዲያ አማራጮች በመኖራቸው የአውሮፓ ህብረትንም ሆነ የአሜሪካ ባለስልጣናት ለጥቁር ህዝቦች ያላቸውን ንቀት፣ ጣልቃ ገብነትና የተዛባ የሚዲያ ዘመቻ ለአለም ለማሳየት ምቹ መሆኑን ገልጸዋል።
በተፈጠረው ምቹ ሁኔታም ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ምእራባውያን ከፈጠሩላቸው የጥላቻ ታሪክ በመውጣት በመላው አለም ተቃውሟቸውን ማሰማታቸው የአሜሪካ ባለስልጣናትን ማበሳጨቱንም ነው ዶክተር ሲሞን የገለጹት።