በኢትዮጵያ የንፁህ መጠጥ ውኃና የንጽህና አገልግሎት ተደራሽነት ላይ የሚሰራ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የንፁህ መጠጥ ውኃና የንጽህና አገልግሎት ተደራሽነት ላይ የሚሰራ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በስድስት ክልሎች ተግባራዊ የሚሆን የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦትና የጽዳት አገልግሎት ፕሮጀክት ይፋ ሆነ።
ለፕሮጀክቱ 41 ሚሊዮን ዩሮ የተመደበ ሲሆን 18 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዩሮ የፊንላንድ መንግሥት ቀሪውን 22 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዩሮ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት ሸፍኗል።
ፕሮጀክቱ በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በደቡብ፣ በሲዳማና በትግራይ ክልል በሚገኙ 99 ወረዳዎችና 37 ዞኖች ላይ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል።
ለቀጣይ ሦስት ዓመታት በሚካሄደው በዚሁ ፕሮጀክት ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሰዎች በላይ የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት እንዲያገኙ እንደሚደረግም ተገልጿል።
ፕሮጀክቱ በማኅበረሰቡ የሚመራ ሁሉን አቀፍና አስተማማኝ የገጠር ውኃ አቅርቦትና የቤተሰብ የንጽህና አገልግሎት ተደራሽነት ለማስፋትም ትኩረት ያደርጋል ተብሏል።
የዘርፉ መሰረተ ልማት ዝርጋታ እንዲሳለጥ፣ የሴቶች የዘርፉ ተሳትፎ እንዲጎለብትና የመረጃ ቅብብሎሽ ሥርዓቱ እንዲጠናከርም በፕሮጀክቱ እቅድ ተቀምጧል።
የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ነጋሽ ዋጌሾ፤ ፕሮጀክቱ የገጠሩን አካባቢ የንጹህ ውኃ አቅርቦት ለማሻሻል ይረዳል ብለዋል።
በአካባቢው ሁሉን አቀፍ የንጽህና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ትኩረት መደረጉንም ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ የፊንላንድ አምባሳደር ኡቲ ሆሎፔነን በበኩላቸው አገራቸው በኢትዮጵያ የንጹህ መጠጥ ውኃና የንጽህና አገልግሎት ለማስፋት የሚደረገውን ጥረት እየደገፈ መሆኑን ገልጸዋል።
አሁን የተጀመረው አዲስ ፕሮጀክትም አገራቸው ለአመታት ስትሰራበት የቆየች መሆኑን ተናግረው ፕሮጀክቱ የገጠሩን ማኅበረሰብ ትኩረት ማድረጉን ነው የገለጹት።
ያም ብቻ ሳይሆን ተደራሽ ያልሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ያማከለ መሆኑን ጠቁመዋል።
አገራቸው በኢትዮጵያ የዘርፉን እድገት ለመደገፍ የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።
ፊንላንድ ከኢትዮጵያ ጋር በመተባበር የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦትና የንጽህና አገልግሎትን ለማሻሻል ባለፉት 27 ዓመታት ከኢትዮጵያ ጋር ስትሰራ መቆየቷ ተገልጿል።
የኢትዮጵያና ፊንላንድ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተጀመረው እኤአ በ1959 መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።