በኢትዮጵያ ላይ የሚደረግ ማንኛውም የውጭ ሀገራት ጣልቃ ገብነት በጋራ ማስቆም ይገባል- የህንድ ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊያን - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ላይ የሚደረግ ማንኛውም የውጭ ሀገራት ጣልቃ ገብነት በጋራ ማስቆም ይገባል- የህንድ ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊያን
አዲስ አበባ ግንቦት 19/2013/ኢዜአ/ በኢትዮጵያ ላይ የሚደረግ ማንኛውም የውጭ ሀገራት ጣልቃ ገብነት በጋራ በመመከት ማስቆም የሁሉም ሃላፊነት ሊሆን ይገባል ሲሉ የህንድ ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን ገለጹ።
ኢትዮጵያ በመጪው ክረምት ከምታከናውናቸው ትላለቅ ኩነቶች መካከል አንደኛው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነው።
ታዲያ እነዚህን ትልልቅ ጉዳዮች ተከትሎ በአሁኑ ሰዓት የውጭ ጣልቃ ገብነት እየተበራከተ መሆኑ በስፋት እየተስተዋለ መጥቷል።
የሀገራቱን ጣልቃ ገብነት ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ባሉበት ሆነው እየተቃወሙ እና እያወገዙ ይገኛሉ።
በአዲስ አበባ የሚኖሩ የህንድ ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያንም በኢትዮጵያ ላይ የሚስተዋለውን የውጭ ሀገራት ጣልቃ ገብነትን አውግዘዋል።
ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እየገቡ ያሉ አገራት ከኢትዮጵያ ጋር ለረጅም ዓመታት ግንኙነት ያላቸው መሆኑን ጠቅሰው በውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ በመግባት ታሪካዊ ግንኙነቱን ሊያበላሹ አይገባም ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም ሰላም ጉልህ ሚና ያላት ሀገር መሆኗን የጠቀሱት አስተያየት ሰጪዎቹ የውጭ ሃይሎች የኢትዮጵያን ጉዳይ ለኢትዮጵያውያን መተው አለባቸው ብለዋል።
ትውልድ እና እድገቱ በአዲስ አበባ ከተማ የሆነው ህንዳዊው ሀርሽ ኮታሪ፤ በሉዓላዊ አገር ላይ ጣልቃ ገብተው የራሳቸውን አጀንዳ ለማስፈፀም የሚሰሩ ሀገራትን በአንድነት በመቆም መመከት ይገባል ብለዋል።
በአዲስ አበባ ተወልደው ያደጉት ሌላኛው የህንድ ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ከውሸል ካሺሻንት ሼት፤ በኢትዮጵያ ላይ በውጭ ኃይሎች የሚደረጉ ተጽዕኖዎችን በዲፕሎማሲያዊ ጥረት መመከት ይገባል ብለዋል።
ነዋሪነታቸውን በእንግሊዝ ሀገር ያደረጉት ትውልደ ኢትዮጵያዊ ዳንኤል ወልደ ሥላሴ በበኩላቸው
ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ትክክለኛና የጠራ መረጃ እንዲያገኝ በመገናኛ ብዙኃን በኩል የተጠናከሩ ሥራ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
አሁን በኢትዮጵያ እየደረሰ ያለውን የውጭ ተጽዕኖ እና ኢ-ፍትሃዊነት ከመቼውም ጊዜ በላይ በአንድነት በመቆም ችግሩን መወጣት አለብን ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።