ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ባለፉት ሰባት አመታት ለህዳሴ ግድብ ከ252 ሚሊዮን ብር በላይ የቦንድ ግዥ ፈጽሟል - ኢዜአ አማርኛ
ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ባለፉት ሰባት አመታት ለህዳሴ ግድብ ከ252 ሚሊዮን ብር በላይ የቦንድ ግዥ ፈጽሟል
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19/2013 (ኢዜአ) ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ባለፉት ሰባት አመታት ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ከ252 ሚሊዮን ብር በላይ የቦንድ ግዥ መፈጸሙን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤልገለጹ።
ኮሚሽኑ በዛሬው እለት የህዳሴ ግድብ የገቢ ማሰባሰቢያ ዋንጫን በኮሚሽኑ ከወንጀል መከላከል ዘርፍ ለወንጀል ምርመራ ዘርፍ አስረክቧል።
በርክክቡ የኮሚሽኑ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፤ ያለንበት ጊዜ ለዘመናት በህዝባችን ላይ የተዘረጋውን አፈና እና ጭቆና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እያስወገድንበት ያለንበት ወቅት ነው ብለዋል።
የሁለተኛው ዙር የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት እንዳይሳካ የውስጥና የውጭ ጠላቶች ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና በማድረግ ላይ መሆናቸውን አንስተዋል።
በተጨማሪ አገር ለማፍረስ ቅጥረኞችን በማስታጠቅ ላይ ታች እያሉ ይገኛሉ ብለዋል።
በመሆኑም የፌዴራል ፖሊስ አባላት በኢትዮጵያ ህልውና ላይ የሚቃጡ ማናቸውንም የፀረ ሰላም ሃይሎች እንቅስቃሴ ለመመከት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
ከግድቡ መሰረት መጣል ጀምሮ በግንባታው ሂደት ፌዴራል ፖሊስ አባላት ያልተቋረጠ ጥበቃ እያደረጉ እንደሚገኙም ገልጸዋል።
በቀጣይም በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች እና አባላት የህዳሴው ግድብ ከፍጻሜ እንዲደርስ የፀጥታ ስራውንና ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
በሌላ በኩልም ለ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ ሂደት የፖሊስ አባላት ሌት ተቀን እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው ይህንኑ ተግባራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።
በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል መከላከል ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፈንታ በበኩላቸው የህዳሴው ግድብ የሁሉም ኢትዮጵያዊ አሻራ ያረፈበት የሉአላዊነታችን እና የአንድነታችን መገለጫ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህ የህዝብ ፕሮጀክት ደህንነት የፌዴራል ፖሊስ አባላት ሌት ተቀን እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
የህዳሴ ግድብ የገቢ ማሰባሰቢያ ዋንጫ ወደ ዘርፉ ከመጣ በኋላ ባወጣው እቅድ መሰረት ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ እንደተሰባሰበ ጠቅሰዋል።
የፖሊስ አባላት ለዘንድሮው ምርጫ ፍትሃዊና ሰላማዊ ሂደት በገለልተኝነት እንዲከናወን እየሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሄራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ የፖሊስ አባላት በፀጥታ ስራና በገንዘብ መዋጮ ጭምር እያደረጉ ላሉት ጉልህ አስተዋፆ አመስግነዋል።
የሰራዊቱ አባላት እስካሁን እያደረጉት ላለው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው እስከ ግድቡ ፍጻሜ ድረስ ሁሉም ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።
የግድቡ ግንባታ አሁን ላይ 80 በመቶ መድረሱን ጠቅሰው ግድቡ የአንድነታችንን ምሰሶ የሚገነባ" ነው ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የህዳሴ ግድብ የገቢ ማሰባሰቢያ ዋንጫን የወንጀል መከላከል ዘርፍ ለወንጀል ምርመራ ዘርፍ አስረክቧል።