በትራፊክ ቁጥጥር አዳዲስ አሰራሮች ተግባራዊ መደረጋቸው ውጤት አስገኝቷል... የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ - ኢዜአ አማርኛ
በትራፊክ ቁጥጥር አዳዲስ አሰራሮች ተግባራዊ መደረጋቸው ውጤት አስገኝቷል... የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 19/2013(ኢዜአ) በትራፊክ ቁጥጥር አዳዲስ አሰራሮች ተግባራዊ በመደረጋቸው በትራፊክ አደጋ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱን የአዲስ አበባ ከተማ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ አስታወቀ።
ኤጀንሲው ለኢዜአ በላከው መግለጫ በተያዘው በጀት ዓመት የፍጥነት ወሰንና የደህነት ቀበቶ አጠቃቀም ቁጥጥርን ጨምሮ በትራፊክ ድህንነት ላይ ያተኮሩ 65 ተግባራት ገቢራዊ መሆናቸውን አመላክቷል።
ተግባራቱ በትራፊክ አደጋ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እንዲቀንስና በቁጥጥር ሂደት የተሻለ ውጤት መታየቱን አስታውቋል።
በምህንድስናው ዘርፍ የትራፊክ ደህንነትን የሚያረጋግጡ ዘርፈ ብዙ ማሻሻያዎች መከናወኑም ለውጤቱ አስተዋፆ አድርጓል ተብሏል።
በመዲናዋ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በትራፊክ አደጋ የተመዘገበው የሞት ቁጥር 287 መሆኑን የጠቀሰው መግለጫው፤ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ18 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል።
በትራፊክ አደጋ የሚደርሰው ከባድ የአካል ጉዳትም በ10 በመቶ ቀንሷል።
በመዲናዋ በትራፊክ አደጋ ከሞቱ ሰዎች ቁጥር 80 በመቶ የሚሆኑት እግረኞች መሆናቸውም በመግለጫው ተመላክቷል።
በትራፊክ አደጋ የሚደርሰውን የሞትና የአካል ጉዳት ለመቀነስ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ጤና ቢሮ፣ ትምህርት ቢሮ፣ የደንብ ማስከበር ጽህፈት ቤትና ሌሎች ባለድርሻ አከላትን ያሳተፈ ስራ እየተከናወነ መሆኑም ተገልጿል።
በመዲናዋ በትራፊክ አደጋ የሚደርሰውን ሞት ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ባለበት ማቆምና፤ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ መቀነስ መቻሉን ከአዲስ አበባ ከተማ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።