የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ሰበሰበ

አዲስ አበባ ግንብት 19/2013/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን አስታወቀ።

የትራንስፖርት ሚኒስቴር በሥሩ ያሉ ተጠሪ ተቋማት እያከናወኑ ያሉትን የመንገድ፣ የባቡር፣ የደረቅ ወደብ አገልግሎት እና የመሠረተ ልማት ሥራዎች ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እያስጎበኘ ይገኛል።


ከተጠሪ ተቋማቱ የተጎበኘው የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት መስከረም 24 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ የ24 ሰዓት የክፍያ መንገድ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑ ተገልጿል።

በመሆኑም ባለፉት 7 ዓመታት 46 ሚሊዮን የተሽከርካሪ ፍሰት በማስተናገድ ከ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማገኘቱ ታውቋል። 

መንገዱ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር በቀን በአማካይ 8 ሺህ ተሽከርካሪዎች ያስተናግድ የነበረው ተቋሙ አሁን ላይ በቀን በአማካይ ከ26 ሺህ በላይ በላይ የተሽከርካሪ ምልልሶችን ለማስተናገድ መቻሉ ተነግሯል።

ኢንተርፕራይዙ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡም ተገልጿል።

ገቢው የተገኘው ከክፍያ መንገድ አገልግሎት፣ ከማስታወቂያ፣ ከመንገድ ጉዳት ካሳ ከተሽከርካሪ ማንሻና መጎተቻ ክፍያ እንደሆነም ነው የተገለጸው።

በአሁኑ ወቅት ከ300 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያላቸውን የክፍያ መንገዶች የሚያስተዳድረው ኢንተርፕራይዙ ለ679 ዜጎች ቋሚ እና ለ192 ዜጎች ጊዜያዊ የስራ ዕድል ፈጥሯል።

የመንገድ መሰረተ ልማት ለገቢና ወጪ ንግድን ለማሳለጥ ጉልህ ሚና እንዳለው እና ከአገልግሎቱ በሚገኘው ገቢ የመንገድ ተደራሽነትን ለማስፋፋትም እንደሚረዳ ነው የተገለፀው ።

በቀጣይነትም ግንባታቸው ተጠናቆ የሚረከባቸውን የክፍያ መንገዶች ለማስተዳደር አሁን ላይ የተገኙ ተሞክሮዎችን በመቀመር፤ የታዩ ውስንነቶችን መገምገም እና በማስተካከል ሀገራዊ ተልዕኮውን ለመፈፀም እየሰራ እንደሆነ ተገልጿል።

ሌላው የጉብኝቱ አካል የነበረው የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የአየር ክልል ደህንነት አሁን ካለበት ይበልጥ አስተማማኝ እንዲሆን እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኮሌኔል ወሰንየለህ ሁነኛው እንዳሉት፤ ተቋሙ ከዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ፈጣን ዕድገት ጋር አብሮ ለመራመድ የሚያስችሉ ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኑን አብራርተዋል።

ለጅቡቲ፣ ሶማሊያ እና ሶማሌ ላንድ አገራት የአየር ትራፊክ ቁጥጥር ሥልጠና እየሰጠ እንደሆነም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም