ቀጥታ፡

“ሽብርተኛው ድርጅት ሕወሓትን ከመንግስት ጋር በተመሳሳይ ረድፍ ለማስቀመጥ መሞከር ተቀባይነት የለውም”… ሴናተር ጂም ኢንሆፍ

ግንቦት 19 ቀን 2013(ኢዜአ) የኢትዮጵያ መንግስትን ከሽብርተኛው ድርጅት ሕወሓት ጋር በተመሳሳይ ረድፍ ለማስቀመጥ መሞከር ተቀባይነት የለውም ሲሉ የአሜሪካው ሪፐብሊካን ፓርቲ ሴናተር ጂም ኢንሆፍ አስታወቁ።

ሴናተር ጂም ኢንሆፍ በአሜሪካ የእንደራሴዎች ምክር ቤት የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ያላቸውን ሀሳብ አቅርበዋል።

ሴናተሩ ባቀረቡት ጽሁፍ “የኢትዮጵያ መንግስት ሁሉንም ሰላማዊ መፍትሔዎችን ለማምጣት እየሰራ ይገኛል፤ ሰላምንና አንድነትን ከማምጣት ውጪ ሌላ አካሄድ አልሄደም” ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እንደተነገረው በትግራይ ክልል የተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ ወንጀለኞችን ለሕግ የማቅረብ ተግባር ነው ያሉት ሴናተር ኢንሆፍ “በዚህ ሁኔታ በአገሪቱ ሰላምን ለማምጣት እየተንቀሳቀሰ የሚገኘውን መንግስት ከሽብር ድርጅቱ ህወሓት ጋር በእኩል ማስቀመጥ ተቀባይነት የሌለው ነው” ብለዋል።

በዋናነትም መታወቅ ያለበት ጉዳይ “ህውሓት የሽብር ድርጅት” መሆኑ ነው ሲሉ አጽንዖት ሰጥተው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን ለ19 ጊዜያት ያህል ጎብኝቻለሁ ያሉት ሴናተሩ፤ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር በነበራቸው ቆይታ መንግስት በአገሪቱ አንድነትንና ሰላምን ለማምጣት እየሰራ መሆኑን መነጋገራቸውን አመልክተዋል።

በተለይም የኢትዮ ኤርትራን ግንኙነት ዳግም በመመለሳቸው የአለም የሰላም ኖቤል ተሸላሚ መሆናቸውን አስታውሰወው፤ መንግስት ለቀጠናው ሰላምና ደህነንነት እያከናወነ ያለውን ተግባር አስገንዝበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ በአዲስ መልክ ካቢኔያቸውን አቋቁመው በሁሉም አካባቢ ወደ ስራ በሚገቡበትም ወቅት የሽብርተኛው ድረጅት ደስተኛ እንዳልነበር አስታውሰው፤ የህወሓት የሽብር ቡድን ግን ከማእከላዊ መንግስት ጋር ያለውን ግንኙነት በማቋረጥ ወደ ግጭት መግባት ጀመረ ብለዋል።

በጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በአገሪቱ መከላከያ ጦር ላይ ጥቃት መፈጸሙን ገልጸው፤ መንግስትም ይህንን ተከትሎ ወደ ሕግ ማስከበር ዘመቻ ገብቷል ሲሉ አስረድተዋል።

በዚህ ወቅት የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችና ጥፋቶችን ለመመርመርና ተጠያቂነትን ለማምጣት የኢትዮጵያ መንግስት ከተመድ እና ሌሎች አጋር አካላት ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆኑንና ይህንንም እየተገበረ ይገኛል ብለዋል።

የአሜሪካ መንግስትም ይህንን ሂደት በመደገፍ ከኢትዮጵያ ጎን ሊቆም ይገባል ሲሉ አመልክተዋል።

ለኢትዮጵያውያን እና ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “እየሰራችሁ ያላችሁትን ስራ እንደግፋለን አብረናችሁ ነን ለማለት እወዳለሁም” ሲሉ አጋርነታቸውን ገልጸዋል።

በትላንትናው እለት ሴናተር ጂም ኢንሆፍ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልእክት "የባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ ያሳለፈውን የቪዛ እገዳዎችን እቃወማለሁ'' ማለታቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም