ኢትዮጵያን "የአፍሪካ ኢኖቬሽን መዳረሻ" ለማድረግ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን "የአፍሪካ ኢኖቬሽን መዳረሻ" ለማድረግ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ ግንብት 19/2013/ኢዜአ/ ኢትዮጵያን "የአፍሪካ ኢኖቬሽን መዳረሻ" ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።
"አዲሷን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መዳረሻ ኢትዮጵያን እናስስ" በሚል ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎችና የአሜሪካ ባለሃብቶች የተሳተፉበት የበይነ መረብ ውይይት ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ ኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት እየሰራቻቸው ያሉ ስራዎች በሚመለከታቸው አካላት ተብራርተዋል። በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍፁም አረጋ መንግስት ምቹ የንግድ ከባቢ ሁኔታን ለመፍጠርና የውጭ ባለሃብቶችን ለመሳብ የተለያዩ የህግ ማሻሻያዎች እያደረገ መሆኑን ነው የገለጹት።
በግሉ ዘርፍ የሚመራ ኢኮኖሚን ለመገንባትም የንግድ ህግ ማሻሻያ መደረጉንና የኢንቨስትመንት አዋጅ መውጣቱን አምባሳደሩ ተናግረዋል። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አህመዲን መሐመድ (ፒ ኤች ዲ) ኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችላትን የዘርፉን ማሻሻያዎች በማድረግ የዲጂታል መሰረት እየጣለች መሆኑን አስረድተዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው እንዳሉት ኢትዮጵያ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂና የኤሌክትሮኒክስ ትራንዛክሽን አዋጅ መፅደቁ፣ የዲጂታል መታወቂያ ወደ ትግበራ መግባት፣ የስታርት አፕና የግል መረጃ ጥበቃ አዋጅ በረቂቅ ሂደት ላይ መሆናቸው፣ የመንግስት የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎትና ኢኮሜርስ ላይ በልዩ ትኩረት እየሰራች ነው።
በዚህም ኢትዮጵያን "የአፍሪካ ኢኖቬሽን መዳረሻ" የማድረግ እቅድ ያለው ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የዲጂታል ቴክኖሎጂ አማካሪ ሜሪያም ሰይድ ኢትዮጵያ ከመንግስት መር ኢኮኖሚ በግሉ ዘርፍ ወደሚመራ ኢኮኖሚ ሽግግር እያደረገች መሆኑን አሳውቀዋል።
የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚው ተዋናይ እንዲሆን ለማድረግም የንግድ ስራ ቅልጥፍና ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው ያሉት አማካሪዋ የቴሌኮም ዘርፉን በከፊል ወደ ግል የማዞር ስራ፣ የዲጂታል ክህሎት ግንባታ፣ የመረጃ መረብ ደህንነት ጥበቃ፣ የግለሰብ የመረጃ ጥበቃ አዋጅ ለዘርፉ መደላልድል ለመፍጠር እየተሰራባቸው መሆኑን አብራርተዋል።
የአሜሪካ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ እየተደረገ ያለውን የዘርፉን ማሻሻያ እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቀርበዋል።