በኢትዮጵያ ደካማና ተላላኪ መንግስት ለመፍጠር የሚሹ ሀገራት አይሳካላቸውም --የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ደካማና ተላላኪ መንግስት ለመፍጠር የሚሹ ሀገራት አይሳካላቸውም --የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች
ግንቦት 18 ቀን 2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ደካማና ተላላኪ መንግስት ለመፍጠር የሚሹ ሀገራት ጥረታቸው ፍፁም የማይሳካ መሆኑን የክልል ርእሳነ መስተዳድሮች ገለጹ።
"ኑ ኦሮሚያን እናልብሳት" የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የክልሉ ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ እንዲሁም የተለያዩ የክልል ርእሳነ መስተዳድሮች በተገኙበት ተጀምሯል።
በዚሁ መርሃ ግብር ላይ የተናገሩት ርእሳነ መስተዳድሮቹ ኢትዮጵያ ደካማና ተላላኪ መንግስት ለመፍጠር የሚሹ ሀገራት ጥረታቸው ፍፁም የማይሳካ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን አንድነት ለመከፈፈልና በትንንሽ ክልሎችና ደካማ አገር ለመፍጠር የሚያደርጉት ጥረት ተቀባይነት የሌለውና የተሳሳተ አካሄድ መሆኑንም ተናግረዋል።
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ፤ የውጭ ሃይሎች በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላማዊ ሽግግር እንዳይኖርና ደካማ መንግስት ለመፍጠር እየሰሩ ስለመሆኑ ገልጸዋል።
በድጋፍ ሰበብ የአገሪቱን ሉአላዊነት ለመድፈር የሚያደርጉት ጥረት ተቀባይነት የሌለውና ፍፁም የማይሳካ መሆኑንም ተናግረዋል።
ሁላችንም በአንድነት ፊታችችን ወደ ልማት በማዞር ከውጭ አገራት ጥገኝነት እራሳችንን ለማላቀቅ መስራት ይኖብናል ብለዋል።
ስንዴ እየሰጡ ለዘመናት በድህነት ውስጥ እንድንኖር የሚሹ ሀገራት መኖራቸውን ጠቅሰው ከዚህ ለመውጣት በትብብር ጠንክረን መስራት ይኖርብናል ብለዋል።
ከውጭ አገር ስንዴ አንለምንም፣ አንቀበልም በዚህ ዓመት በቴክኖሎጂ የተደገፈ የአስተራረስ ስልት በመጠቀም ምርትና ምርታማነት ላይ የሰራናውንና ውጤት ያገኘንበትን ስራ አጠናክረን እንቀጥላለን ነው ያሉት።
የውጭ ጣልቃ ገብነት አንቀበልም፣ በአገር ውስጥ በርካታ ምርት በማምረት የውጭ ምንዛሬን ለማስፋት እንስራለን ሲሉም ጠአረጋግጠዋል።
የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር አቶ አገኘው ተሻገር በበኩላቸው ደካማና ተላላኪ መንግስት ለመፍጠር የሚሹ ሃይሎች ጥረታቸው ፍፁም አይሳካም ብለዋል።
የውጭ ኃይሎች የኢትዮጵያን አንድነት በመሸርሸር ደካማ አገር ለመፍጠር የሚያደርጉትን ጥረት ሁላችንም በመረዳት በጋራ መመከት አለብን ብለዋል።
የአገር ውስጥ ተላላኪ ባንዳዎችን በአንድነት ሆነን በጋራ ልንታገላቸው ይገባልም ነው ያሉት።
የውጭ ሃይሎች ለዘመናት ኢትዮጵያ በራሷ ሀብት እንዳትጠቀምና ከድህነት እንዳትወጣ ያደርጉት የነበረውን ጥረት አሁንም ቀጥለውበታል ያሉት ደግሞ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳው ናቸው።
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ላዴሞ በበኩላቸው የአሜሪካ መንግስት በተደራደሩ ሰበብ የሞተውን ስርዓት ከመቃብር ለማንሳት የሚያደረገው ጫና ተቃባይነት የለውም ብለዋል።
በዚህ ሰበብ በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገው ጫና ተቀባይነት የሌለው ድርጊት በመሆኑ ሁችንም በጋራ ልናወግዘው ይገባል ብለዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ ይሞላል፣ ምርጫውም በጋራ ጥረታችንና በህዝቡ ድጋፍ ስኬታማ ይሆናል ብለዋል ርእሳነ መስተዳድሮቹ።