ቀጥታ፡

አርቲስት ፈቃዱ ተክለማርያም በኪነ ጥበብ ቤተሰቦች አንደበት

አዲስ አበባ ሀምሌ 26/2010  ባለፉት 43 ዓመታት በኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ መድረኮች ነግሶ ያለፈው አርቲስት ፈቃዱ ተክለማርያም በዛሬው ዕለት በቅድሰት ሥላሴ ካቴድራል ስርዓተ ቀብሩ ተፈጽሟል። የቀብር ስነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተው ሃዘናቸውን ሲገለጹ የነበሩ የኪነ ጥበብ  ቤተሰቦችና የቅርብ ወዳጆቹም ስለ አንጋፋው የጥበብ ሰው ሰብዕና ለኢዜአ አስተያየታቸውን ገልጸዋል። ከእነዚህም መካከል አርቲስት መርሻ ጌታሁን፣ ተዋናይ ደሳለኝ ኃይሉ፣ አርቲስት ችሮታው ከልካይና መምህር ሁሴን መሃመድ እንዲህ ይናገራሉ። አርቲስት መርሻ ጌታሁን  በሰጡት አስተያየት "ትልቅ የጥበብ ሰው ነበር፣ መካሪ ነው፤በጥበብ  ሕይወቴ እያለሁ እኔ አንድም ቀን ከሌላ ሰው ጋር ሲጣላ አይደለም ክፉ ሲነጋገር ሰምቼ አላውቅም” ብለዋል፡፡ “ከጥበብ ግንኙነታችን በተጨማሪ ከእምነትና ሃይማኖት ጋር በተያያዘ ወንድሜ ፣ መካሪዬና አጽናኜ ነው ። የሚሰራውን ስራ በዕውቀት ነው የሚሰራው። ችሎታ አለው፤የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያውቀው ነው።  በጣም ትልቁ ሰዋዊና ሙያዊ ስነ ምግባር ያለው ሰው ነው።” ያለው ደግሞ አርቲስት ደሳለኝ ኃይሉ ነው፡፡ አርቲስት ችሮታው ከልካይ በበኩሉ ”ፈቃዱ ለኔ ሙሉ ሰው ነው። በሁሉም ነገር እግዚአብሄር ጸጋውን ያደለው ሰው ነው። በስነ ምግባር ከሰው ጋር በመግባባት፣ በማህበራዊ ኑሮ፣ በሙያ፣ይሄ የተሟላላት ሰው እድለኛ ሰው ነው “ የኪነ ጥበብ ቤተሰቦቹ ከተወዳጁ የጥበብ ሰው ፈቃዱ ተክለማርያም ፈለጉን ሊከተሉትና ሊማሩት የሚገባ ሙያዊ ትምህርት እንዳለም ይጠቅሳሉ። አርቲስት መርሻ ጌታሁን "ወጣቶች ከሱ ብዙ መማር አለባቸው። እንኳን እነሱ እኔም እየተማርኩ ነው በሕይወት እስካለሁ ድረስ፤ መድረክ ላይ እስከሰራሁ ድረስ የሱን ፈለግ ተከትዬ ነው ማደግ እምፈልገው።ብሏል፡፡ አርቲስት ደሳለኝ ኃይሉ “ብዙዎቻችን የሌለን ልንማር የሚገባው  በሙያውና ሰዋዊ ስነ ምግባሩ ሁልጊዜ ስናስታውሰው ስንዘክረው የምንኖረው ነው።” አርቲስት ችሮታው ከልካይ “ አርቲስት የሚነግሰው/ዝናን የሚያገኘው ማህበረሰቡ፣ ህዝቡ ሲቀበለው ነው። ይህን ፍቅር ለማግኘት በሰከነ ምግባር መታነጽ፤ ሰውን ማክበር፣ ሃገርን መውደድ፣ ከምንም በላይ ህዝብና አገርን መውደድ ነው።” “ከሱ መማር የምንችለው የትወና ብቃት፣ ደግነት፣ ርህራሄን፣ ስጦታን፣ ከሰው ጋር መልካም ሆኖ የመኖርን ዘዴ እነዚህ ነገሮች መማር አለብን።” ያለው  መምህር ሁሴን መሃመድ ነው፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም