ቀጥታ፡

የ"ብሔራዊ ክብር በሕብር" አስተባባሪ ኮሚቴ ከብሪታኒያ ኤምባሲ ተወካዮች ጋር ውይይት አደረገ

ግንቦት 18 ቀን 2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ላይ እየደረሰ ያለውን የውጭ ጣልቃ ገብነት በመቃወም የተቋቋመው የ"ብሄራዊ ክብር በህብር" አስተባባሪ ኮሚቴ በአዲስ አበባ ከሚገኘው የብሪታኒያ ኤምባሲ ተወካዮች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አደረገ።

የመርሃ ግብሩ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት በብሪታኒያ ኤምባሲ በነበራቸው ቆይታና የውጭ ጣልቃ ገብነትን በመቃወም እያከናወኗቸው ባሉ ስራዎች ላይ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ከተለያዩ ታዋቂ ግለሰቦችና አርቲስቶች የተቋቋመው የ"ብሔራዊ ክብር በሕብር" አስተባባሪ ኮሚቴ በአዲስ አበባ የብሪታኒያ ኤምባሲ በመገኘት ያዘጋጀውን ደብዳቤ መልዕክቱን ለኤምባሲው ተወካዮች አድርሷል።

የኮሚቴው አባላት ደብዳቤውን ከማድረስ በተጨማሪ ከኤምባሲው የፖለቲካ አታሼ (ባለሙያና) እና ቆንሱል ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ውይይት አድርገዋል።

የአስተባባሪ ኮሚቴ አባል አቶ አቢይ ታደለ፤ ግንቦት 13 ቀን 2013 ዓ.ም ለኤምባሲዎች ሊደርስ የነበረው ደብዳቤ ኤምባሲዎች ዝግ በመሆናቸው ምክንያት በዕለቱ ደብዳቤን ማስገባት አለመቻሉን ገልጸዋል።

ኤምባሲዎቹ ቀጠሮ በሚሰጡ ጊዜ ደብዳቤን ለማስገባት እቅድ ተይዞ እንደነበረና የብሪታኒያ ኤምባሲ ዛሬ ረፋድ ላይ በሰጠው ቀጠሮ መልዕክቱ እንደደረሳቸውና ከኤምባሲው ተወካዮች ጋር ውይይት መደረጉን ገልጸዋል።

በደብዳቤው ላይ የውጭ አገራት የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የሕዝቦች እኩልነት ማክበር እንደሚገባቸው፣ ከተሳሳተ መረጃ እንዲርቁ፣ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የለውጥ ጉዞ በግልጽ እንዲረዱ መገለጹን ተናግረዋል።

ከብሪታኒያ ኤምባሲ በተጨማሪ ለአሜሪካ ኤምባሲና በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት ልዑክ ጽህፈት ቤት ደብዳቤዎቹን ለማድረስ እቅድ የነበረ ቢሆንም ቀጠሮ ስላልሰጡ መልዕክቱን ማድረስ አለመቻሉን አመልክተዋል።

በኤምባሲውና በጽህፈት ቤቱ ቀጠሮ ለማግኘትና ለመወያያት በኢሜል መልዕክቶች ቢላኩም ቀጠሮ ለማግኘት አልተቻለም ብለዋል።

ስልክ በመደወል ቀጠሮ ለማስያዝ ጥረት ቢደረግም ስልክ ቁጥሮች ቀጠሮ ለማስያዝ አገልግሎት እንደማይውሉ ለመረዳት መቻሉን ገልጸዋል።

ኮሚቴው ያሉትን አማራጮች ለመጠቀም ለአሜሪካ ኤምባሲና በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት ልዑክ ጽህፈት ቤት በአድራሻቸው ደብዳቤው በፖስታ ቤት በኩል እንዲላክ መደረጉን ተናግረዋል።

አሁንም የኮሚቴው አባላት ከሁለቱ አካላት ጋር ውይይት ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸውና የደብዳቤውን ምላሽ እንደሚጠብቁ ነው አቶ አቢይ ያስረዱት።

የውጭ ጣልቃ ገብነቱን በመቃወም "እጃችሁን ከኢትዮጵያ ላይ አንሱ" በሚል መሪ ሀሳብ ከግንቦት 12 ቀን 2013 ዓ.ም የዲጂታል ፊርማ መሰባሰቢያ መርሃ ግብር እየተደረገ እንደሚገኝና ለአንድ ወር ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ ገልጸዋል።

ሁሉም ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ የማህበራዊ ትስስር ገጽ አማራጮች ተጠቅመው ፊርማውን በመፈረም ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ አቶ አቢይ ጥሪ አቅርበዋል።

የ"ብሔራዊ ክብር በሕብር" አስተባባሪ ኮሚቴ በቀጣይ ሌሎች መርሃ ግብሮችን እንደሚያዘጋጅና ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርክ አክለዋል።

ሌላኛው የ"ብሔራዊ ክብር በሕብር" አስተባባሪ ኮሚቴ አባል ደራሲ አበረ አዳሙ ከብሪታኒያ ኤምባሲ ተወካዮች ጋር በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ፣ ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ፣ በትግራል ክልል ባለው ሁኔታ፣ ኢትዮጵያን አስመልክቶ በሚሰራጩ የተሳሳቱ መረጃዎችና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ውይይት መደረጉን ገልጸዋል።

የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ኢትዮጵያ ግድቡን የምትገነባው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እነጂ ሌሎች አገራትን የመጉዳት ፍላጎት እንደሌላትም አስረድተዋል።

የትግራይ ክልል ያለውን ሁኔታ አስመልክቶም የብሪታኒያ መንግስት መሬት ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በግልጽ መረዳትና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎች መራቅ እንደሚገባው በውይይቱ ላይ መነሳቱን ተናግረዋል።

ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ እንዲሆን እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን አስመልክቶ ገለጻ እንደተረገም አመልክተዋል።

በውይይቱ ወቅት የኤምባሲው ተወካዮች የብሪታኒያ መንግስት አጠቃላይ ምርጫው ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ እንዲሁን ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።

ለትግራይ ክልል ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ለመረዳት የመንግስታቸው ተወካዮች በክልሉ ጉብኝት እንዳደረጉ ያለውን እውነታ ለመረዳት እንዳስቻላቸው በውይይቱ ላይ ማንሳታቸውን ነው ደራሲ አበረ ያብራሩት ።

የአስተባባሪው ኮሚቴ አባላት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምና ሉዓላዊ ክብር በአንድነት መቆም እንደሚገባው ገልጸዋል።

ሁሉም ዜጋ እኔ ከሚለው ይልቅ እኛ የሚለውን እሳቤ በመያዝ ኢትዮጵያ እየገጣሟት ያሉትን ጫናዎችና ፈተናዎች በጋራ ሆኖ በመመከት ለአገሩ ዘብ መሆን ያለበት ጊዜ አሁን ነው ብለዋል።

የ"ብሔራዊ ክብር በሕብር" አስተባባሪ ኮሚቴ ግንቦት 13 ቀን 2013 ዓ.ም ከቀኑ 10 እስከ 11 ሰዓት ድረስ የሚቆይ "ከኢትዮጵያ እጃችሁን አንሱ" በሚል መሪ ሀሳብ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በያሉበት ሆነው ድምጻቸውን ያሰሙበት ዝግጅት ማካሄዱ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም