ቀጥታ፡

ሴቶች ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ተላቀው የስራ እድል ፈጣሪ የሚሆኑበት እድል ሊመቻችላቸው ይገባል- ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

ግንቦት 18/2013 (ኢዜአ) ሴቶች ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ተላቀው ስራ ፈጣሪ የሚሆኑበት ሰፊ እድል ሊመቻችላቸው እንደሚገባ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ አሳሰቡ።

ፕሬዝዳንቷ ይህን ያሉት የሴቶች ኢንተርፕሩነርሺፕ ልማት ፕሮጀክት የሁለተኛ ዙር መርሃ ግብር ማስጀመሪያ መድረክ ላይ ነው።

ፕሮጀክቱ በዋናት የብድር አገልግሎት በማቅረብና ስልጠናዎችን በመስጠት ሴቶችን በኢኮኖሚ የማብቃት ስራ ላይ የሚያከናውን ሲሆን፤ በባለፉት ሰባት ዓመታት በተገበረው የመጀመሪያው መርሃ ግብር ከ17 ሺህ በላይ ሴቶችን ተጠቃሚ አድርጓል።

ሁለተኛው ዙር የሴቶች ኢንተርፕረነርሽፕ ልማት ፕሮጀክት "የሴት ባለሃብቶችን ማፍራት የብልጽግና መሰረት ነው!" በሚል መሪ ሃሳብ  ዛሬ ይፋ ተደርጓል።

በመድረኩም የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባላት፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የዓለም ባንክ ተወካዮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ በሚገኙ በ18 የተለያዩ ከተሞች እንደሚተገበርና ለዚሁ ስራም ከዓለም ባንክ የ100 ሚሊዮን ብር ድጋፍ መገኘቱ ተገልጿል።

ባለፉት ሰባት ዓመታት በተተገበረው የመጀመሪያ ዙር መርሃ ግብር በርካታ ሚሌነር እንስቶችን ማፍራት መቻሉም በመድረኩ ተመላክቷል።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፤ በዚሁ ወቅት ለሴቶች በቂ የስራ እድል ባለመመቻቸቱ ምክንያት ኢትዮጵያ የሚገባትን ያህል የኢኮኖሚ ጥቅም እያገኘች አለመሆኑን ተናግረዋል።

በመጀመሪያው ዙር የተተገበረው መርሃ ግብር በማህበረሰቡ ውስጥ ለዓመታት ተንሰራፍቶ የቆየውን የሴቶች የኢኮኖሚ ጥገኝነት በመቅረፍ ረገድ ጉልህ ሚና መጫወቱንም ነው የተናገሩት።

መርሃ ግብሩ ሴቶች ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ተላቀው ለማህበረሰባቸው በማስቻል ረገድ አኩሪ ስራ ማከናወኑንም እንዲሁ።

በቀጣይም ሴቶች የገንዘብ አያያዝና ንግድ አስተዳደር ክህሎታቸውን ማዳበር እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

የከተማ ልማትና ኮንስትራከሽን ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ፤ ሴቶች ድጋፍ ከተደረገላቸው ስራቸውን በስኬት የሚመሩ መሆናቸውን ፕሮጀክቱ በግልጽ አሳይቷል ብለዋል ።

ይህም በሴቶች ተጠቃሚነት ላይ የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች ውጤታማነት ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

ከፍተኛ ውድድርና ጥንካሬን በሚጠይቀው የንግድ ስራ ላይ በውስን መነሻ ካፒታል ሚሌኒየር የሆኑ ሴቶችን ማፍራት መቻሉንም ነው ያነሱት።

የሴቶችን ችሎታ በማጎልበት በኢንቨስትመንት ተሰማርተው ሃብት እንዲያካብቱ ለማድረግ አማራጮች ሁሉ ክፍት ናቸው ያሉት ደግሞ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሪት ያስሚን ወሃብረቢ ናቸው።

የፌደራል ስራ እድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ዋና ዳሬክተር አቶ ገብረመስቀል ጫላ፤ የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ሴቶች ከራሳቸው አልፈው ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በመርሃ ግብሩ የተካተቱ ሥራ ፈጣሪ ሴቶች ተጨማሪ የሰው ኃይል የመቅጠር አቅማቸው ከ55 በመቶ፤ የድርጅታቸው ትርፋማነት ደግሞ ከ44 በመቶ በላይ እድገት ማስመዝገቡንም ገልጸዋል።

የመጀመሪያው ዙር የሴቶች ኢንተርፕረነርሽፕ ልማት ፕሮጀክት በአራት ክልሎች በሚገኙ 10 ከተሞች መተግበሩ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም