ቀጥታ፡

ለፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ በተደረገው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር በታየው ተሳትፎ ኮርተናል- የክለቡ ፕሬዚዳንት

ግንቦት 18/2013 (ኢዜአ) ለፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ በተደረገው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ከኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በታየው ተሳትፎ ኮርተናል ሲሉ የክለቡ ፕሬዝዳንት ገለጹ።

ለፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ ትናንት በተካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጨምሮ የክልል ርእሳነ መስተዳድሮች፣ ባለሃብቶችና የስፖርት ቤተሰቦች ተሳትፈዋል።

በገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግበሩም ከባለሃብቶች፣ ከተለያዩ ክልሎችና ስፖርት ወዳድ ግለሰቦች ከ170 ሚሊዮን ብር በላይ ቃል ተገብቷል።

የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ ፕሬዚዳንትና የጎንደር ከተማ ከንቲባ ሞላ መልካሙ፤ በገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሩ በኢትዮጵያዊነት ስሜት በነበረው ተሳትፎና ድጋፍ ኮርተናል ብለዋል።

ፋሲልን ለሻምፒዮንነት ያበቃው ከኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ለክለቡ የፈረሙ ተጫዋቾች ለአንድ ዓላማ ለድል በመቆማቸውና በጋራ በመስራታቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊያን በሀገራቸው ጉዳይ በጋራና በትብብር ከሰሩ የማይቻል ነገር የለም ያሉት አቶ ሞላ በገቢ ማሰባሰቡ ሂደት የታየው ተሳትፎ ሁላችንንም ያኮራ ነው ብለዋል።

በአዲስ አበባ ትናንት በተካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ መድረክ የየክልል አስተዳዳሪዎችና ባለሃብቶች በገቡት ቃል ከ170 ሚሊዩን ብር በላይ መገኘቱን ገልጸዋል።

ከኦሮሚያ ክልል 25 ሚሊዮን ብር ፣ ከአማራ ክልል 20 ሚሊዮን ብር፣ ከደቡብ ክልል 10 ሚሊዮን ብር፣ ከሱማሌ፣ ከአፋርና ሲዳማ ክልሎች ደግሞ እያንዳንዳቸው 5 ሚሊዮን ብር ቃል መገባቱን ጠቅሰዋል።

ከአማራ፣ ከትግራይ፣ ከኦሮሚያና ሌሎችም ክልሎች የተለያዩ ባለሀብቶች ለፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ ድጋፍ ማድርጋቸውንም ገልጸዋል።

በገቢ ማሰባሰብ ሂደቱ ከታሰበው ዓላማ አንጻር የተሳካ ነበር ሲሉም የክልቡ ፕሬዝዳንት ገልጸዋል።

በቀጣይም በባህር ዳርና ጎንደር እንዲሁም ሌሎች ከተሞች መሰል የገቢ ማሳባሰቢያ ዝግጅቶች ይካሄዳል ብለዋል።

የ2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪሚሪሊግ አሸነናፊው ፋሲል ከነማ በቀጣዩ ዓመት ኢትዮጵያን ወክሎ በአፍሪካ ሻምፒዮንስሊግ ተሳትፎው  የገንዘብ አቅም ክፍተት እንዳይፈጠር የሚያደርግ ነው።

ድጋፉ ለሻምፒዮንስሊግ ተሳትፎና የእግር ኳስ አካዳሚ ግንባታ ጥሩ መነሻ የሆናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም