ቀጥታ፡

ፕሮሶፒስ ጁሊፍሎራል የተባለውን መጤ አረም አማራጭ የኃይል አቅርቦት ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ ግንቦት 18/2013(ኢዜአ) የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብአቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት፤ ፕሮሶፒስ ጁሊፍሎራል የተባለውን መጤ አረም አማራጭ የኃይል አቅርቦት ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረመ ።

በሳይንሳዊ አጠራሩ ፕሮሶፒስ ጁሊፍሎራል በመባል የሚጠራው መጤ አረም በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ድርቅ በሚያጠቃቸው የተለያዩ አካባቢዎች በስፋት ይገኛል።

አረሙ በሶማሌና በአፋር ክልሎች በስፋት ሲገኝ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች በተወሰኑ አካባቢዎች ላይ ተስፋፍቶ ይገኛል።

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በድምሩ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በአረሙ መወረሩን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በተለይ በአፋርና ሶማሌ ክልሎች የተሰራጨው አረም የግጦሽና የእርሻ መሬትን በመውረር ጉዳት እያደረሰ መሆኑ ይታወቃል።

አረሙ በአንድ አካባቢ ያለን ውሃ እስከ 53 ሜትር ድረስ የሚደርሱ ሥሮችን በመዘርጋት በአካባቢው የሚገኝ ውሃን ሙሉ በሙሉ በመውሰድ አካባቢውን ለድርቅ እንደሚያጋልጥም ተመልክቷል።

አረሙ በቀን እስከ 36 ሊትር፣ በዓመት ደግሞ እስከ 3 ነጥብ 3 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ይወስዳል።

በአረሙ በሚወሰደው ውሃ ከ460 ሺህ ሄክታር በላይ የሸንኮራና ከ330 ሺህ ሄክታር በላይ የጥጥ ማሳዎችን ማልማት የሚያስችል ነው።

በመሆኑም ይህንን መጤ አረም አማራጭ የኃይል ምንጭ ለማድረግ የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብአቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ፕሪንዝ ጂ ኤም ቢ ኤች ከተባለው የጀርመን ኩባንያ ጋር ስምምነት ተፈራርሟል።

በስምምነቱ መሰረት ኢንስቲትዩቱ አረሙን ወደ ኃይል የሚቀይርባቸውን ማሽኖች ለመግዛት የሚያስችለው ይሆናል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ዮሐንስ ድንቃየሁ በዚሁ ወቅት እንዳሉት አረሙን በኃይል ምንጭነት መጠቀም አማራጭ የኃይል አቅርቦትን የሚያሰፋ ነው።

በኢንዱስትሪዎች በተለይም በሲሚንቶ ኢንዱስትሪ የሚስተዋለውን የኃይል አቅርቦት ችግር ለማቃለል አስተዋጽኦ ያደርጋልም ብለዋል።

ስምምነቱ የውጭ ምንዛሪን ለማዳንና ለሥራ ፈጠራ ሚና እንደሚያበረክት ገልጸው፣ በአረሙ ተይዞ የነበረውን ቦታ መልሶ በማልማት ለእርሻ እንደሚውል ገልጸዋል።

የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብአቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ሀላላ አረሙ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ አረሙን ወደ አማራጭ ኃይልነት ለመለወጥ አምስት ዓመታት ጥናት ማድረጉን ተናግረዋል።

በጥናቱም ከአረሙ የሚመነጨው ኃይል ለሲሚንቶ ኢንዱስትሪዎች የድንጋይ ከሰልን በመተካት አገልግሎት እንደሚሰጥ መረጋገጡን አስታውቀዋል።

በዚሀም ከውጭ የሚገባውን የድንጋይ ከሰል 40 በመቶ በመቀነስ በዓመት 120 ሚሊዮን ዶላር ማዳን ያስችላል ብለዋል።

በኃይል አቅርቦት ደረጃም ከዚህ ቀደም ጥቅም ላይ ከሚውለው 24 ሚሊዮን ኪሎ ዋት ኃይል ማትረፍ እንደሚቻልም አቶ ሳሙኤል አስረድተዋል።

ስምምነቱ አረሙን ከሥሩ በመንቀል፣ በማጨድና በመፍጨት ወደ ኢንዱስትሪዎቹ የሚያደርሱ ማሽኖችን ከኩባንያው ለ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዩሮ ለመግዛት እንደሚያስችል ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም