ቀጥታ፡

ማኅበራቱ የኅብረተሰቡን የቅድመ ምርጫ ግንዛቤ ለማሳደግ እየሰሩ መሆኑን ገለጹ

አዲስ አበባ ግንቦት 18/2013 (ኢዜአ) በቅድመ ምርጫ ወቅት በኅብረተሰቡ ዘንድ የሚኖረውን ግንዛቤ ለማሳደግ እየሰሩ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የሲቪክ ማሕበራት ድርጅቶች ገለጹ።

በምርጫው ድምፅ መስጫ ዕለት ሒደቱን በገለልተኝነት ለመታዘብ መዘጋጀታቸውንም አስታውቀዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት የሲቪክ ማኅበራት መካከል የኢትዮ ቲክ ታንክ ግሩፕ ምክትል ማኔጀር ዶክተር ጌትነት አስራት ምርጫው ሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ሕብረተሰቡን ከወዲሁ የማንቃት ስራ እየሰራን ነው ብለዋል።

ማኅበሩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ያቋቋሙት በመሆኑ በተለይ ተማሪዎች በአገራቸው ጉዳይ 'ያገባኛል' ብለው እንዲሳተፉ የሚያደርግ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።

ወጣቶች በመጪው አገራዊ ምርጫ ምክንያታዊ ተሳትፏቸውን እንዲያጎለብቱ የሚያደርጉ ስልጠናዎችን እየሰጡ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የማኅበሩ አባላት በምርጫ ወቅትም ሆነ ከምርጫው በኋላ አገሪቷ የተረጋጋችና ሠላማዊ እንድትሆን ሕብረተሰቡን በማንቃት ረገድ የበኩላቸውን ለመወጣት እየጣሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።

የፊደል ብርሃን በጎ አድራጎት ድርጅት ስራ አስኪያጅ አቶ ብሩክ ገመቹ ማሕበሩ ምርጫውን የመታዘብና የሕብረተሰቡን ግንዛቤ የማጎልበት ስራ በበጎ ፈቃድ ለማከናወን ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም የምርጫ ፕሮጀክት ቀርጸን ወደ ስራ ገብተናል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ኅብረት ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ አበራ ኃይለማሪያም ስለ ምርጫው የግንዛቤ ክፍተት እንዳይኖር ከእድሮች ጋር በመቀናጀት ሲሰሩ መቆየታቸውን አውስተዋል።

ኅብረቱ በጎዳናዎች ላይ በመዘዋወር ኅብረተሰቡ ተሳትፎውን እንዲያጎለብት በበራሪ ወረቀቶች፣ በድምጽና በተለያዩ የቅስቀሳ አማራጮች ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እያከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ለ45 አገር በቀል የሲቪክ ማኅበራት ድርጅቶች 6ኛውን አገራዊ ምርጫ እንዲታዘቡ ፈቃድ መስጠቱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም