በአማራ ክልል የሚወዳደሩ ፓርቲዎች ከተመደበላቸው አየር ሰዓት 66 ነጥብ 7 በመቶውን ብቻ ተጠቅመዋል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የሚወዳደሩ ፓርቲዎች ከተመደበላቸው አየር ሰዓት 66 ነጥብ 7 በመቶውን ብቻ ተጠቅመዋል
ባህርዳር ግንቦት 18/2013 (ኢዜአ) -በአማራ ክልል የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከተመደበላቸው የአየር ሰዓት ውስጥ እስካሁን 66 ነጥብ 7 በመቶውን ብቻ መጠቀማቸውን የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን አስታወቀ።
በክልሉ ከሚወዳደሩ 18 የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ስድስቱ የተመደበላቸውን የአየር ሰዓት ሙሉ በሙሉ ያልተጠቀሙ መሆናቸው ተመልክቷል።
በኮርፖሬሽኑ የምርጫ ዴስክ አስተባባሪ አቶ አስማማው በቀለ ለኢዜአ እንደገለጹት የፖለቲካ ፓርቲዎች ፕሮግራማቸውን በሚዲያ እንዲያስተዋውቁ የተፈቀደው ህዝቡ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ምርጫ እንዲያካሂድ ነው።
ኮርፖሬሽኑ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በመድረክ በማገናኘት የሚያካሂዱትን ክርክርና ውይይት እንዲሁም የአደባባይና የመድረክ ቅስቀሳቸውን በመዘገብ መረጃውን ለህዝብ እያደረሰ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣንና የምርጫ ቦርድ በመደበላቸው ነጻ የአየር ሰዓት በመጠቀም አማራጭ ፕሮግራማቸውንና ፖሊሲያቸውን ለህዝብ እንዲያቀርቡ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ከመጋቢት 30 ቀን 2013 ዓም ጀምሮ በአንድ ወር ውስጥ በአማራ ቴሌቪዥን ከተመደበላቸው 1ሺህ 845 ደቂቃ እስካሁን 1ሺህ 275 ደቂቃውን ብቻ መጠቀማቸውን አመልክተዋል።
ቀሪውን 570 ደቂቃ እንዳልተጠቀሙበት አስረድተዋል።
በተጨማሪም የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በአማራ ራዲዮ ከተመደበላቸው 1ሺህ 560 ደቂቃ ውስጥ መጠቀም የቻሉት 1ሺህ 005 ደቂቃውን ብቻ መጠቀማቸውን ተናግረዋል።
በቴሌቪዥንና ራዲዮ ከተመደበላቸው አጠቃላይ ደቂቃ ውስጥ መጠቀም የቻሉት 66 ነጥብ 7 በመቶውን ብቻ መሆኑን በማሳያነት አቅርበዋል።
በክልሉ ከሚወዳደሩ 18 የፖለቲካ ፓርቲዎች ስድስቱ የተመደበላቸውን የአየር ሰዓት ሙሉ በሙሉ ያልተጠቀሙ መሆናቸውንም አመልክተዋል ።
የአየር ሰዓቱን ያልተጠቀሙት የኢትዮጵያ ነጻነት ፓርቲ፣ የአገው ብሄራዊ ሸንጎ፣ የቅማንት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ህብረትና የአርጎባ ብሄረሰብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ናቸው።
የተመደበላቸውን የአየር ሰዓት በአግባቡ ከተጠቀሙ ውስጥ ብልጽግና፣ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሃይል ንቅናቄ (አዴሃን)፣ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን)ና ሌሎች እንደሚገኙበት አመልክተዋል።
አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የምርጫ ስነ ምግባር ደንቡን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የጋራ ቃል ኪዳን ሰነድና የአገሪቱን ህጎች የሚጻረሩ መልዕክቶችን በማምጣታቸው አስተካክሉ ሲባሉ በዛው የቀሩ እንዳሉም አስረድተዋል።
በማያያዝ በበኩር ጋዜጣ ተጠቅመው ዓላማና ፕሮግራማቸውን እንዲያስተዋውቁ ከተመደበላቸው 24 ኮለመን ውስጥ ዘጠኝ ኮለመኑን አለመጠቀማቸውን አስገንዝበዋል።
"እጅግ ውድ የሆነውን የሚዲያ የአየር ሰዓት የፖለቲካ ፓርቲዎች አለመጠቀማቸው ተገቢነት የለውም" ያሉት አቶ አስማማው የአየር ሰዓቱ ለመዝናኛ፣ ለማስተማሪያና ለማስታወቂያ ቢውል የሚያስገኘውን ገቢ ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል።
ሚዲያው ከሌሎች ተግባራት በማስበለጥ መራጩ ህዝብ ፓርቲዎች በሚያቀርቡት ሃሳብና መልዕክት መረጃ አግኝቶ ለሀገርና ለህዝብ ይጠቅማል የሚለውን ፓርቲ በምክንያታዊነት እንዲመርጥ የተሰራው ስራ አበረታች መሆኑን ገልጸዋል።
ፓርቲዎች የተመደበላቸውን የአየር ሰዓት እንዲጠቀሙ በስልክና ሌሎች መገናኛ መንገዶች እየተነጋገሩ መሆኑን የገለጹት አቶ አስማማው በቀጣይ መልዕክታቸውን በመላክ እንዲጠቀሙ አሳስበዋል።
በሀገራችን ለ6ኛ ጊዜ የሚካሄደው ምርጫ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም እንዲካሄድ መወሰኑ የሚታወስ ነው።