ቀጥታ፡

ደቡብ ሱዳን ህዳሴ ግድብን በተመለከተ በአፍሪካ ኅብረት የሚካሄደውን የሦስትዮሽ ድርድሩ ትደግፋለች - አምባሳደር ጀምስ ፒቲያ ሞርጋን

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2013 ( ኢዜአ) ደቡብ ሱዳን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ

ግድብን በተመለከተ በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት የሚካሄደውን የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የሦስትዮሽ ድርድር እንደምትደግፍ በኢትዮጵያ የአገሪቱ አምባሳደር ጀምስ ፒቲያ ሞርጋን ገለጹ።

"ኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን ሠላም አዋላጅ ነች" ሲሉም አምባሳደሩ ገልጸዋል።


ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ካላት ትልቅ ሚና አኳያ የውስጧን ሰላም በማስጠበት የቀጠናውን ምጣኔ ኃብታዊ ትስስር ልትመራ እንደሚገባትም አምባሳደሩ ተናግረዋል።

አምባሳደር ጀምስ ፒቲኣ ሞርጋን፤ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት የናይል ውኃ የሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት የጋራ ሃብት በመሆኑ ሁሉም ያለምንም ችግር ሊጠቀምበት ይገባል።

በውኃው ላይ የሚካሄዱ ፕሮጀክቶች ልማታዊ ጎናቸው መታየት አለበት ያሉት አምባሳደሩ ችግሮች ካሉም ሀገራቱ በሰላማዊ መንገድ መፍታት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ የሚነሱት ውዝግቦችም በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ሦስቱ አገራት ወደ ዘላቂ መፍትሄ መምጣት እንደሚችሉ ነው የጠቆሙት።

የአፍሪካ ኅብረት ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት የሚያስችል ቁመና እያለው ለመንግሥታቱ ድርጅትም ሆነ ለሌላ አካል ጣልቃ እንዲገባ መፍቀድ አያስፈልግም ብለዋል።

አፍሪካ ኅብረትም የታዛቢነት ሚና ሳይሆን በጉዳዩ ላይ ሥልጣን እንዳለው በመረዳት ሁነኛ መፍትሄ ለመሥጠት መሥራት እንደሚገባው ነው አምባሳደሩ የተናገሩት።

ኅብረቱ ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ የሚለውን መርህም እውን ማድረግ ይጠበቅበታል ብለዋል።

በሌላ በኩል "ኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን ሠላም አዋላጅ ነች" ያሉት አምባሳደሩ ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን ሠላም ግንባታ የመጀመሪያ ረድፍ ተሰላፊ ሀገር ናት ብለዋል።

ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን የሰላም ጉዳይ ተስፋ ሳትቆርጥ ሀገራቸው አሁን ላለችበት ሰላምና መረጋጋት እንድትደርስ አበርክቶዋ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችሉ የአየር፣ የባቡርና የመንገድ መሰረተ ልማቶችን የመክፈትና የማጠናከር ሥራ ትኩረት መደረጉንም ጠቁመዋል።

ይህንንም በተመለከተ ከሚመለከተው ከኢትዮጵያ ተቋምና ከከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ጋር ውይይት ተደርጎ የመግባቢያ ሥምምነት ሠነድ መፈራረማቸውን ተናግረዋል።

በተጓዳኝም ኢትዮጵያ በአከባቢው ካላት ሚና አኳያ ውስጣዊ ሰላሟን በሟስጠበቅ የቀጠናውን ኢኮኖሚያዊ ትስስር በቀዳሚነት ልትመራ እንደሚገባ ነው የገለጹት።

ቀጠናው የሚከተለው ነጻ የሰዎች ዝውውርን ጨምሮ የኢትዮጵያ ሁኔታ ላይ የተመሰረተ መሆኑንም ነው የጠቀሱት።

ኢትዮጵያ ቀጣናውን በምጣኔ ሃብት ማስተሳሰር ከቻለች የቀጠናው አገራት ወደ ልማትና እድገት የመምራት እድሏ ከፍተኛ መሆኑን አምባሳደሩ ተናግረዋል።

ደቡብ ሱዳን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2013 ከገባችበት የእርስ በእርስ ጦርነት አገግማ አሁን ላይ ወደ ቀደመ ሰለሟ እየተመለሰች ትገኛለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም