በኢትዮጽያ ከሁለት አመት በፊት በደረሰው የአውሮፕላን አደጋ ሰብአዊነት ያሳዩ ሰዎች "የሰውነት ተምሳሌቶች" ናቸው በሚል እየተመሰገኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጽያ ከሁለት አመት በፊት በደረሰው የአውሮፕላን አደጋ ሰብአዊነት ያሳዩ ሰዎች "የሰውነት ተምሳሌቶች" ናቸው በሚል እየተመሰገኑ ነው
ግንቦት 18/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጽያ ከሁለት አመት በፊት በደረሰው የአውሮፕላን አደጋ ህይውታቸው ያለፉ ሰዎችን ያከበሩና ሰብአዊነታቸውን ያሳዩ ሰዎች "የሰውነት ተምሳሌቶች" ናቸው በሚል ሰላም ሚኒስቴር የምስጋና መድረክ እያካሄደ ነው።
በመድረኩ የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚልን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ታድመዋል።
መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ከጥዋቱ 2.00 መነሻውን ከአዲስ አበባ አድርጎ ወደ ናይሮቢ ሲበር የነበረ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ ማክስ - 8- 737 አውሮፕላን በምስራቅ ሸዋ ዞን ግምቢቹ ወረዳ ቱሉ ፈራ ቀበሌ ተከስክሶ 157 አገራት ዜጎች ሕይወት ማለፉ አይዘነጋም።
አዳጋው ሲደርስ የግምቢቹ አካባቢ ነዋሪዎች ቀድመው ወደ አደጋው ስፍራ በመድረስ የሟቾችን አስከሬን ጠብቀዋል፣ በእንባ እየተራጩም ሀዘናቸውን መግለፃቸው ይታወሳል።
ከዕለቱ ጀምሮም ተጎጂዎችን በማሰብ 7፣ 12፣ 40፣ 80፣ መንፈቅና ዓመታት ተዝካር በማውጣት ከፍ ያለ የሰብዓዊነት ተግባርም በተከታታይ ፈፅመዋል።
አውሮፕላኑ የተከሰከሰበት ስፍራ የእርሻ ማሳ ቢሆንም የሰዎች ደም የፈሰሰበትን አናርስም በሚል እንዲከለል አድርገው በክብር ታጥሮ እንዲቀመጥ አድርገዋል።
እርሙን ማውጣት የሚሻ የተጎጂ ቤተሰብ፣ ወዳጅ ዘመድ እየመጣ ሀዘኑን እንዲገልጽም ምቹ ሁኔታ ፈጥረዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች ለአደጋው የተቆረቆሩበትና ሀዘናቸውን የገለፁበት መንገድ እንዲሁም ሰብአዊነታቸው የብዙዎችን ቀልብ የሳበና ያስደነቀ ተግባር ሆኖ አልፏል።
በመሆኑም ለዚህ ሰዋዊ ተግባራቸው ሰላም ሚኒስቴር "የሰውነት ተምሳሌት" በሚል በዛሬው እለት በስፍራው የምስጋና መድረክ አዘጋጅቷል።
በስነ ስርአቱ ላይ የአካባቢው ነዋሪዎች ሚኒስትሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የተጎጂ ቤተሰቦችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።