የኢትዮጵያን ህልውና የሚፈታተኑ ውስጣዊና ውጫዊ ጫናዎችን በጋራ መመከት ያስፈልጋል- የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ህልውና የሚፈታተኑ ውስጣዊና ውጫዊ ጫናዎችን በጋራ መመከት ያስፈልጋል- የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን ህልውና የሚፈታተኑ ውስጣዊና ውጫዊ ጫናዎችን በጋራ መመከት ያስፈልጋል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተናገሩ።
ኢትዮጵያ ለየትኛውም የውጭ ጫና ሉአላዊነቷን አሳልፋ አትሰጥም ሲሉም ገልጸዋል።
ኢዜአ በስልክ ያነጋገራቸው የብልፅግና፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት፣ የህዳሴ እንዲሁም የኢትዮጵያ ነጻነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ከየትኛውም ጊዜ በላይ አሁን የኢትዮጵያን ህልውና የሚፈታተኑ ችግሮችን ለመመከት በጋራ የምንቆምበት ወቅት ላይ እንገኛለን ብለዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት የአለም አቀፍና ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ፤ በኢትዮጵያ የተካሄደውን የህግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻ ተከትሎ የራሳቸው ፍላጎት ያላቸው አገራት በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ፍላጎትና ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
እንዲህ አይነት አካሄዶች በጋራ ፍላጎትና ጥቅም ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ያላቸውን አገራት ግንኙነት የሚያሻክር ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።
አጋጣሚዎችን በመጠቀም የመንግስትን እጅ ለመጠምዘዝ ሙከራዎች መደረጋቸውን ጠቅሰው ''የትኛውም የውጭ ጫና ቢመጣ ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን አሳልፋ አትሰጥም" ብለዋል።
የአሜሪካ አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ ያሳለፈው ውሳኔ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአካባቢው ሀገራት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድር መሆኑንም አብራርተዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያን ህልውና የሚፈታተኑ ውስጣዊና ውጫዊ ጫናዎችን በጋራ መመከት ያስፈልጋል ብለዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ምሁራን እና ዜጎች ያላቸውን ልዩነት ወደ ጎን በመተው ይህን ፈታኝ ጊዜ በትብብር ማለፍ ይገባቸዋልም ነው ያሉት።
በተለይ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተደራጁት ህዝብና አገር ስላለ በመሆኑ በውስጣቸው ያለውን ልዩነት በማቻቻል በአገር ሉዓላዊነት ላይ በጋራ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት ፓርቲ ፕሬዝዳንት ዘሪሁን ገብረእግዚአብሄር ''የአገር ጉዳይ ምንጊዜም አይለየንም፣ በኢትዮጵያ ላይ የሚመጡ ጫናዎች በሙሉ የአገሪቷን ሉዓላዊነት የሚፈታተን በመሆኑ በጽኑ እናወግዛለን'' ብለዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የኢትዮጵያን ህልውና የሚፈታተኑ ውስጣዊና ውጫዊ ሃይሎችን እንደ አንድ ሆነው መመከት ይገባቸዋልም ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ ላይ የሚጣሉ ማዕቀቦች ባለስልጣናትን ብቻ ሳይሆን አገርን የሚጎዱ በመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ልዩነታችንን ወደ ጎን ጥለን ለአገር አንድነት በጋራ መስራት አለብን ብለዋል።
የህዳሴ ፓርቲ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ኤሊያስ ዘሪሁን፤ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚፈታተኑ የውጭ ጫናዎች ከጥንት ጀምሮ እንደነበሩ አስታውሰዋል።
ይሁንና ''ህዝቦቿ በአንድነትና በጋራ ክንዳቸው መክተው በከፈሉት መስዋዕትነት ነጻነቷንና ክብሯን ጠብቃ ቆይታለች'' ብለዋል።
አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያ ለየትኛውም የውጭ ጫና ሉአላዊነቷን አሳልፋ አትሰጥም ሲሉ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያና አሜሪካ የረጅም ጊዜ አጋር እንደመሆናቸው በተለይ የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ የሚወስናቸው ውሳኔዎች ግንኙነቱን ሊያሻክር የሚችል መሆኑን ጠቅሰዋል።
በአሁን ጊዜ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት የሚሞክሩ ሃይሎች መኖራቸውን ጠቅሰው እንዲህ አይነት ድርጊትን የፖለቲካ ልዩነትን ግምት ውስጥ ሳናስገባ መመከት አለብን ብለዋል።
የኢትዮጵያ ነጻነት ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ግዛቸው አመራ፤ የአሜሪካ አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ችኩልነት የታየበትና የአገሪቷን ነባራዊ ሁኔታ ግምት ወስጥ ያላስገባ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገር ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮች ላይ ተወያይተው የጋራ መፍትሄ ማምጣት ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።