ቀጥታ፡

በምስራቅ የሀገሪቱ ከተሞች የአራተኛው ትውልድ የኢንተርኔት አገልግሎት ተጀመረ

ድሬደዋ ፤ግንቦት 18/2013(ኢዜአ) ኢትዮ-ቴሌኮም በምስራቅ የሀገሪቱ ከተሞች የአራተኛው ትውልድ/ 4ጂ/ የኢንተርኔት አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስታወቁ።

ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ  ፍሬህይወት ታምሩ ትናንት ምሽት አገልግሎቱ በድሬዳዋ መጀመሩን  በተበሰረበት መድረክ እንደገለጹት፤ ኢትዮ-ቴሌኮም በሀገሪቱ የሚከናወኑ የምጣኔ ሃብትና የማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ፈጣን ቀልጣፋ እንዲሆኑ መጠነ ሰፊ የሞባል ኔት ወርክ ማስፋፊያ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡

በምስራቁ ከድሬዳዋ ሌላ በሱማሌ ክልል አይሻ  እና በኦሮሚያ ምዕራብ ሐረርጌ ዞን ጭሮ ከተሞችም  የአራተኛው ትውልድ/4ጂ/  ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት መጀመሩን ገልጸው ይህም  በቀጠናው የሚከናወኑ ሁሉን አቀፍ ተግባራት ፈጣን፣ቀልጣፋና ተደራሽ ውጤታማ እንዲሆኑ ያስችላል ብለዋል፡፡

ይህ አገልግሎት ዘንድሮ ብቻ በ103 ከተሞች ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው  በሶስቱ ከተሞች የተጀመረው አገልግሎት ከ330 ሺህ በላይ ደንበኞችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡

በምስራቁ የሀገሪቱ  ከተሞች የአራተኛው ትውልድ ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት መጀመር ስራቸውንና ለደንበኞቻቸው የሚሰጡትን አገልግሎቶች ፈጣንና ቀልጣፋ እንደሚያደርገው የገለጹት ደግሞ ትናንት በድሬዳዋ በነበረው ስርዓት የተገኙት የኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች ገልጸዋል፡፡

የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ ዋና ስራ አስፈጻሚ  ካሚል ኢብራሂም ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በፓርኩ የሚከናወኑ የወጪና ገቢ ንግድ እንቅስቃሴዎችን ውጤታማና ፍሬያማ ለማድረግ አገልግሎቱ ወሳኝ ድርሻ ይኖረዋል፡፡

ዘመኑ የመረጃ ነው ለፈጣን ልውውጥም የተጀመረው አገልግሎት ቁልፍ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የምስራቅ ሪጅን የኢንፎርሜሽን ሲስተም ኃላፊ  ካሳሁን ተካ  በበኩላቸው፤ ቀደም ሲል በቅርንጫፎቹ የሚሰጡ አገልግሎቶች በኢንተርኔት መቆራረጥና አቅም ማነስ ችግር ያጋጥማቸው እንደነበር አስታውሰው አሁን ግን ፈጣንና አርኪ አገልግሎት መስጠት ያስችላል ብለዋል፡፡

በስነ-ስርዓቱ ላይ የድሬደዋ አስተዳደር ምከትል ከንቲባ አህመድ መሐመድና የካቢኔ አባላት ፣ባንኮች፣ ሌሎች የፋይናንስ ተቋማትና የኢንዱስትሪ ባለቤቶች ተገኝተዋል።

ኢትዮ-ቴሌኮም ነገ ደግሞ በተመሳሳይ በሐረር፣ አወዳይ እና ሐረማያ ከተሞች አገልግሎቱ እንደሚጀምርም ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም